Wednesday, October 3, 2012

ዜና ልደቱ ለመምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ ክፍል ሁለት

የሆሣዕና ዕለት ብዙ ሊቃውንት እየተፈራረቁ እንዲያስተምሩና ማኀበሩ እንዲስፋፋ በመዝሙር ,1 ተፈሥሑ በእግዚአብሔር ዘረድአነ፣ በረዳን በእግዚአብሔር ደስ ይበለን ተብሎ ሲመሰገን ውሏል፡፡
   ከዚህም በኋላ ሲያስተምሩ ሰንብተዋል፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እንደራሴ የነበሩት የሐረሩ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የላኳቸው የፓሊስ ኮሎኔልና ሠራዊት የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያን ከበቡት፡፡ በዕለቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምእመናን ጉባዔውን ለመስማት በቤተ ክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት ግጥም ብለው ሞልተው ነበር፡፡
   በእሳተ አደጋ መሥሪያ ቤት አፍዛዣ ባለው የቤተ ክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት መሐል ላይ መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ ከአለቃ ኤልያስ ነቢየ ልዑል ጋር ጎን ለጎን ቆመው ነበር፡፡ መድረኩ ከጣውላ የተሠራ ተንቀሳቃሽ ነው፡፡ የማኅበረ ሥላሴ የድምፅ ማጉሊያን ይዘው የቆሙት አቶ ወልደ ሰንበት የተባሉት የማኀበሩ አባል ነበሩ፡፡
  ከመምህር ገብረ ሥላሴ አጠገብ የፖሊስ አዛዥ ኮሎኔሉ እርሳቸውን ለመያዝ ቆሟል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ሕዝበ ክርስቲያኑ የሃይማኖት መምህራችንን አናስነካም በማለት በቁርጠኝነት ተነሣሥቷል፡፡ ሁኔታው እንዲህ ባለ አስቸጋሪ የደም መፋሰስን የሚያስከትል አደገኛ አዛማሚያ ነበረው፡፡  በዚህን ጊዜ መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ ሕዝቡን ለማረጋጋት  ንግግር አድርገዋል፡፡
 በዕለቱ መምህር ገብረ ሥላሴ ቀይ ከለሜዳ አሸርጠው፣ ወገባቸውን በገምድ አሥረው፣ ጉርድ ነጭ ሸሚዝ ለብሰው፣ በሸሚዙ ላይ የሰንሰለት ቅናት አድርገው፣ በአንድ እጃቸው ከግብረ ሐዋርያት እስከ ራእየ ዮሐንስ የያዘ የግዕዝ ሐዲስ ኪዳን ጨብጠው ሌላውን እጃቸውን በማንሣት የሚከተለውን ንግግር አሰምተዋል፡፡
   ምእመናን ሰማዕትነት አትከልክሉኝ፡፡ እነዚህ ወታደሮች የመጡት ከበላይ ታዘው ነው፡፡ የታዘዙትን እንዳይፈጽሙ አታግዷቸው፡፡ በተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ዘመን ምእመናን መምህራችንን አናስይዝም ብለው ነበር፡፡ ቅዱሱ አባት ግን አልፈቀደላቸውም፡፡ እናንተም እባካችሁ ከወንድሞቻችሁ ከወታደሮች ጋር ጠብን አትፍጠሩ፣ እምቢ ካላችሁ አወግዛችኋለሁ፡፡
     ለመሆኑ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ሞልታችሁ ያላችሁ ምእመናን ሃይማኖታችሁ በትክክል ተዋሕዶ ነውን? ከሆነ እስቲ ቀኝ እጃችሁን ወደ ሰማይ ዘርጉ፡፡ አሏቸው፡፡
    ምእመናንም ዳር እስከ ዳር እጆቻቸውን ያለ ምንም ፍርሃት በጥብዓት ዘረጉ፡፡ በዚህን ጊዜ መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ የሚከተለውን ቃል አሰሙ፡፡
  ምእመናን! እናንተ ለተዋሕዶ ሃይማኖታችሁ ማተባችንን አንበጥስም፣ እምነታችንን አንክድም ብላችሁ እጆቻችሁን አውጥታችኋል፡፡ እግዚአብሔር ከሚመጣው መከራ ሁሉ እጃችሁን ይዞ ያውጣችሁ፡፡ የእናንተ ሰማዕትነት በዚህ ይብቃ፡፡ ከወታደሮች ጋር አትጣሉ፡፡  እንኳን ማሠር ቢገድሉኝም የኃይል ሥራ እንዳትሠሩ አደራ!
በማለት ከተማጸኑ በኋላ የሚከተለውን ኃይለ ቃል አስምተዋል፡፡
የቅዱስ ጳውሎስን መልእክት ምዕራፍ 8 ከቁጥር #5 ጀምሮ ያለውን በመጥቀስ መኑ የኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ … በማለት አዚመዋል፡፡ ከራእየ ዮሐንስም ምዕ፡ 2 ቁጥር 8-%1 ያለውን በመተርጎም፡-
 እሥራት እንጂ ሞት የለብህም ብሎ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጾልኛል፡፡ የእኔስ ፈቃድ በምእመናን መካከል ብሠዋ ነበር፡፡ እናንተ ምእመናን በአንገታችሁ የክርስትና ምልክት ማዕተብ አሥራችኋል፡፡ እኔ ደግሞ አባታችሁ የሰይፉ ማዕተብ ስለተዋሕዶ ሃይማኖት እስካሥር ድረስ ወደ ኋላ አልመለስም፡፡ ኩን መሃይምነ እስከ ለሞት ወእሁበከ አክሊለ ሕይወት[1]፡፡ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ እኔ ገብረ ሥላሴ፣ የሥላሴ ባሪያ ሰማዕተ ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን እሥራት ሞት ወደ ኋላ አይመልሰኝም፡፡ ምእመናን! አንድ ምሥጢር ልንገራችሁ አሁን ፖሊሶቹን የላኩት ቀዳማዊ ዐጤ ኃይለ ሥላሴ ወይም ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ አይደሉም፡፡ ፖሊሶችን የላኩት አቡነ ቴዎፍሎስ ናቸው፡፡
 የተዋሕዶ ሃይማኖት በካምቦሎጆ ልጆች የሚጫወቱባት ኳስ አይደለችም፡፡ እኔ አባታችሁ ገብረ ሥላሴ ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖት እታሠራለሁ፡፡ ለወደፊት ግን ከልዑል እግዚአብሔር አስፈርጄ ስመጣ በዚሁ ዐውደ ምሕረት እንገኛለን፡፡ በዚህች ሃይማኖት ላይ የተነሡ ሁሉ ከቤተ መንግሥት ካሉት ሹማምንት ጀምሮ እነ አቡነ ቴዎፍሎስ ሳይቀሩ ይቀጣሉ፡፡ ይኸ ባይደረግ ገብረ ሥላሴን ሃይማኖት የለህም በሉኝ፡፡ ብለው ንግግራቸውን ፈጸሙ፡፡
  ቀጥሎ የማኅበረ ሥላሴ ሰባኬ ወንጌል ሊቁ አለቃ ኤልያስ ነቢየ ልዑል የሚከተለውን የመጨረሻ የመሰነባበቻ ቃል አሰምተዋል፡፡
ገብሬ! ገብረ ሥላሴ! እኔና አንተ በወንጌል እርሻ እንደ ሁለት በሮች[2] በሕገ ወንጌል ቀንበር የተጠመድን ነበርን፡፡ አንድ ላይ የተጠመዱ በሮች ሊለያዩ አይገባም፣ አብረው ይፈታሉ፣ አብረው ይሠዋሉ፡፡
ገብሬ! ሁለቱን በሮች ባይለያዩን መልካም ነበር፡፡ እኛ ሰማዕትነት ይመጣል ብለን እንጠብቅ የነበረው ካልተጠመቁት ወገኖች ነበር፡፡ ንጉሡም ጳጳሱም እንዲህ ያደርጋሉ ብለን አላሰብንም፡፡ ከሆነማ ሳይለያዩን ሥጋችንንም ምእመናን ገንዘው እንዲቀብሩት አብረው ቢሠውን መልካም ነበር፡፡ ብንሠዋስ ደማችን ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖት በመቆርቆር በንዴት ስላለቀ እንኳን የበሬን ያህል ደም ሊያገኙ የከሲታ አውራ ዶሮ ደም ወጥቶን ያገኙ ይሆን?! አያገኙም!! ካሉ በኋላ በመቀጠል
 ገብሬ! እንዳልከተልህ ዓይነ ሥውር ሆንኩ አብረን እንደተጠመድን አብረን ብንፈታ ይሻል ነበር፡፡ በማለት ልብን የሚነካ ንግግር አድርገዋል፡፡
     መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላም በጸሎት ሕዝቡን ናዝዘው ከፈቱ በኋላ ወታደሮቹን አይዟችሁ እኔ የትም አልጠፋም፣ መጥቼ እጄን እሰጣችኋላሁ፣ ከምእመናን ጋር አትጋጩ፡፡ ብለው ካሳሰቡ በኋላ ሠርሆተ ሕዝብ ሆነ፡፡  
     ሕዝቡ ከተሰናበተ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱንና የፓትርያርኩን እንደራሴ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስን ዘልፈሃል፡፡ ተብለው ሰኔ @9 ቀን 09)%8 ዓ.ም. በፖሊስ ተይዘው ታሠሩ፡፡ በታሠሩበት ቦታ ስንቅ እንዳይቀርብላቸው ታግዶ እህልና ውኃ ሳይቀምሱ እሥረኞቹንና ወታደሮቹን መኮንኖቹን ማስተማር ቀጠሉ፡፡
     ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ መምህር ገብረ ሥላሴ ከእህል ከውኃ  ዘጠኝ ቀን ሙሉ መለየታቸውን ሰምተው ለእርሳቸው እንዲሰጧቸው ንጉሠ ነገሥቱን  አስፈቅደው ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ካልአይ[3] ሊቀ ጳጳስን ልከው ወስደዋቸዋል፡፡
  ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ካልአይ በወቅቱ በመምህር ገብረ ሥላሴ ላይ የሙት በቃ እንዲፈረድባቸው በሚኒስትሮችና ሊቀ ጳጳሳት ጉባዔ እነ አባ ሐና ጅማም ሐሳብ ሲሰጡ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ እኛ ሊቃነ ጳጳሳት መሥራት የሚገባንን ተግባር ሠሩ እንጂ ጥፋት የለባቸውም፡፡ እኛ ፈርተን በአድር ብዬ የተውነውን ሐዋርያዊ ሥራ እርሳቸው ስለፈጸሙ እንኳን የሞት ቅጣት እሥራትና ግዞትም ሊፈጸምባቸው አይገባም፡፡ በማለት ያለ ምንም ፍርሃት ለመምህር ገብረ ሥላሴ እውነተኛነት የመሰከሩ ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡
    በጉባዔ ታይቶ ምንም ወንጀል ባይኖርም በግፍ መተማ ማኅበረ ሥላሴ ገዳም እንዲታሠሩ ተወስኖባቸው በካቴና ታሥረው ሄደዋል፡፡ በሕዝብ ድኀንነቶች እየተጠበቁ በገዳሙ እንዲቀመጡ መደረጉ ለመነኩሴ ገዳም ቤቱ ነው ያሰኛል እንጂ ታሠረ አያሰኝም፡፡ የሚል ጥበብ ያለው ውሳኔ ነው በሚል ተቃውሞ ተነሳሥተው ሌሊትና ቀን በበረሃው እየገሰገሱ በጎንደርና በጎጃም አድርገው በደራ ጕንዶ መስቀል ቆላ ቆላውን ተጕዘው በ 09)%9 ዓ.ም. ደብረ ሊባኖስ ገብተው ግንቦት ፲፪ ቀን ተገልጸው በጉባዔ ሲያስተምሩ ተይዘው በፖሊስ እየተደበደቡ የተዋሕዶ ሃይማኖት ያለህ!!  በማለት የሰማዕትነት ድምፅ እያሰሙ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተደረገ፡፡
    በጊዜው እንዲታሠሩ ለፖሊሶች ያስተወቁት የደብረ ሊባኖሱ ጸባቴ አባ ብጽሐ ጌታሁን[4] ነበሩ፡፡ ጸባቴው ቀድሞ ሻለቃ ለማ በኋላ ግን ኮሎኔል ለማ ለተሰኙት በፍቼ ከተማ የፖሊሰ ሠራዊት አዛዥ ለነበሩት በማስታወቅ መምህር ገብረ ሥላሴን አስይዘው በፖሊሲዎች ድብደባ እየተንገላቱ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ አድርገዋል፡፡
     በጊዜውም መምህር ገብረ ሥላሴን ፖሊሶች በመኪና ጭነዋቸው እየደበደቧቸው ሲወስዷቸው የተዋሐዶ ሃይማኖት ያለህ!! ብለው ድምፃቸውን እያሰሙ በነበረበት ወቅት ብዙ የዓይን ምስክሮች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ምስክሮች መካከል ሰዓታት በመቆም በደብረ ሊባኖስ ያገለግሉ የነበሩት የአለቃ ውብሸት ልጅ አባ ሥዩም ውብሸት ይገኛሉ፡፡
   መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ ከደብረ ሊባኖስ ተይዘው አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ እንደገና ታሥረው መተማ ማኀበረ ሥላሴ ገዳም ተወሰዱ፡፡ የገዳሙ ማኅበርም ሐዋርያ አናሥርም፡፡ በማለታቸው ምክንያት ዳግመኛ መምህር ገብረ ሥላሴ በእግራቸው ተመልሰው አዲስ አበባ ገቡ፡፡
   በጉባዔ ተገልጸው እንደልማዳቸው ወንጌልን ሲሰብኩ በመናገሻ አውራጃ ፖሊስ ወህኒ ቤት  ብዙ ወራት ታሥረው ቆይተዋል፡፡ ከዚያም በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስና በመንግሥት ትእዛዝ በዚያን ጊዜው በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በሚገኘው የዝዋይ ደሴት[5] ውስጥ ብቻቸውን ታሥረው እንዲቆዩ ተጋዙ፡፡
    እርሳቸውም እንደ አባቶቻቸው ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ልዩ እርዳታ ከደሴቱ ወጥተው ሌሊትና ቀን ተጕዘው አዲስ አበባ ገብተው ታማኝ ሎሌ ይሞታል እንጂ አይመለስም፡፡ ብለው በደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ንጉሠ ነገሥቱ ፊት ቀርበው ተናገሩ፡፡ በዚያም ሐዋርያዊ ስብከታቸውን ለምእመናን ሲያስተላልፉ ከዋሉ በኋላ ተይዘው በጥብቅ ትእዛዝ ወደ ዝዋይ  ተመልሰው እንዲጋዙ ተደረገ፡፡ በዚያን ወቅት የአሩሲ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ካልአይ[6] ነበሩ፡፡
  መምህር ገብረ ሥላሴ በግዞት ሳሉ በወቅቱ በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ይማር የነበረው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የመጀመሪያ ምሩቅ አቶ አበራ በቀለ [7] የመምህር ገብረ ሥላሴን ሐሳብ ተረድቶ ይደግፍ ስለነበር በዝዋይ መታሠራቸውን ሰምቶ ከአሜሪካ ዓሣ ማጥመጃና ዓሣ የሚጠበስበት የብረት ድስትና የመሳሰሉትን በገዛ ገንዘቡ ገዝቶ ዝዋይ ድረስ በመሄድ የማጥመድ ስልት አሳይቶ ነፍሳቸውን እንዲያኖሩ ለቁመተ ሥጋ የሚኾናቸውን እርዳታ አከናውኖም ወደ ትምህርት ገበታው መመለሱን በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ራሳቸው መምህር ገብረ ሥላሴ መስክረዋል፡፡
   መምህር ገብረ ሥላሴ በዝዋይ ደሴት አካባቢ የነበሩትን ኢአማንያን አስተምረው ካሳመኑ በኋላ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ መጥተው እንዲያጠምቋቸው ቢልኩባቸው ሊቀ ጳጳሱ መንግሥትንና ቤተ ክህነትን በመፍራት የተጠየቁትን ሳያከናውኑ ቀርተዋል፡፡
  በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ  ቴዎፍሎስና በመምህር ገብረ ሥላሴ መካከል ጠብና መለያየት እንዲስፋፋ ግፊት ያደረጉት ንጉሠ ነገሥቱ መሆናቸውን ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ የዓይን ምስክር በመሆን ስለተረዱ በምሬት ይናገሩ ነበር፡፡
  ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ በወቅቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስንና መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላን በማቀራረብ እንዲስማሙ ለማድረግ መንፈሳዊ ሚና ተጫውተዋል፡፡
    በተጨማሪም የማኅበረ ሥላሴ ሕገ ደንብ በንጉሠ ነገሥቱ እንዲጸድቅ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ከመምህር ገብረ ሥላሴና ከማኅበሩ አባላት ጋር ከንጉሡ ፊት ቀርበው በዝርዝር አብራርተው አስረድተዋቸው ነበር፡፡
   ንጉሡ ግን በተቃራኒው ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ምን ያላደረግንላት አለ?! በማለት በቁጣ ተናገሩ፡፡ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስን በዓይነ መዓት ተመልክተው እናንተን ከማጰጰስ አባ ገብረ ሥላሴን እንዲጳጵስ ብንሾመው ኑሮ ይሻል ነበር፡፡ በማለት የእንግሊዞች የክፋፍለህ ግዛው የመለያየት ፈሊጥ በመጠቀም ሁለቱ አባቶች  እንዲጋጩ አድርገዋል፡፡  የመምህር ገብረ ሥላሴ ዓላማ ጵጵስና መሾም አልነበረም፡፡ ጳጳሳትም ለምን ተሾሙ? የሚል የቅንዓት መንፈስ አልነበራቸውም፡፡
   ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስም የንጉሡን ቁጣ ተመልክተው ከአባ ገብረ ሥላሴ ጋር ለመለያየት የተለያዩ ድርጊቶችን እንደፈጸሙ  ሁለቱንም አበው በቅርብ የሚያውቋዋቸው ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ መስክረዋል፡፡
ሥዕለ ገጽ - 5 መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ በመካከል በስተቀኝ አቶ ኃይለ ልዑል ሀብተ ዮሐንስ በስተግራ የዚያን ግዜው አቶ አበራ በቀለ
 ወደ ተነሣንበት ትረካ ስንመለስ መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ በጽኑ እሥራት በዝዋይ ደሴት አምስት ዓመት ከቆዩ በኋላ ዳግመኛ በመንፈስ ቅዱስ ልዩ ረዳትነትና መግቦት አሁንም በፈቃዳቸው ተመልሰው አዲስ አበባ ገብተው በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለንጉሠ ነገሥቱ ተገልጸው ሲያስተምሩ ውለው በፖሊስ ተይዘው በየካ ምክትል ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ታሥረው ሲሠቃዩ ቆይተዋል፡፡ ከዚያም እንደገና እዚያው ዝዋይ ደሴት በፖሊስ ታጅበው እንዲመለሱ ታዞ አሰላ ላሉት ለክፍለ ሀገሩ ፖሊስ አዛዥ ተሰጡ፡፡ የክፍለ ሀገሩም ፖሊስ አዛዥ ተረክበዋቸው ምክር ለበስ ቃል ከማስጠንቀቂያ ጋር ሰጥተዋቸዋል፡፡
   የፖሊስ አዛዡም በ09)% ዓ.ም. እርስዎ መምህር ገብረ ሥላሴ ታሥረው ወደ ማጂ በአውሮፕላን ሲሄዱ አጅበው ያሳፍሩዎት መኰንን ማን ይባሉ እንደነበር ያስታውሳሉ? ብለው ጠይቀዋቸዋል፡፡ መምህርም አስታውሰው የመኰንኑን ስም ሲነግሯቸው አዛዡ እኔ ነኝ፡፡ ብለው ገልጸውላቸዋል፡፡ ከዚህ በማያያዝም አዛዡ መኰንን አባ ገብረ ሥላሴን አባታችን ለብዙ ዘመን በከባድ ተጋድሎ ቆይተዋል፡፡ ይዘው የሚጓዙት መጽሐፍ ቅዱስ እንጂ መድፍና መትረየስ አይደለም፡፡ ብለዋቸዋል፡፡ በመቀጠልም፡-
 በጥበቃ ልልነት ተለቀው አዲስ አበባ እሥረኛው እንዲመጡ አድርገሃቸዋል፡፡ በማለት ማዕረጌ እንዲገፈፍ ከባድ ወቀሳ ስለደረሰብኝ ከእንግዲህ ወዲህ ከዝዋይ ደሴት ወጥተው ቢገኙ የመግደል እርምጃ እንድወስድ ስለታዘዝሁ ብገድልዎት በእግዚአብሔር ዘንድ በደምዎ ተጠያቂ እሆናለሁ፣ እንዲሁ ብተውዎት ማዕረጌ ተገፎ አዋረዳለሁ፡፡
 ስብከትዎን ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት ካልተቀበሉዎት በሥጋዊ ጦር መሣሪያ የሚዋጉ ስላልሆኑ ዳዊትዎን እየደገሙ በጸሎት ለእግዚአብሔር ያመልክቱ እንጂ  ከዝዋይ ደሴት ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይወጡ አደራ፡፡ በማለት ከማስጠንቀቂያ ጋር ተማጽነዋቸዋል፡፡
  መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላም ሁኔታው እንዲህ ተስፋ የሚያስቆርጥ እርምጃ የሚያስወስድ መሆኑን ተገንዝበው የአዛዡንም ምክር ተቀብለው  እስከ ዛሬ ምርር ያለ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር አላቀረብሁም፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ግን በፍርድ ውሳኔ እስኪ ሰጠኝ ጩኸቴን በጥቡዕ ልቡና በሰቂለ ሕሊና ወደ ፈጣሪዬ አቀርባለሁ፡፡ በማለት መልስ ሰጡ፡፡ ከዚህ በኋላ ከመኰንኑ ጋር በፍቅር ተሰነባብተው ጸሎታቸውን ቀጠሉ፡፡
 በፖሊስ ታጅበው ተመልሰው ወደ ዝዋይ ደሴት ከገቡበት ዕለት ጀምሮ በጣም አስፈሪ በመሆኑ በአካባቢው ሕዝብ ቱሉ ሴጠና -የሰይጣን ኮረብታ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ አፉን ከፍቶ በሚገኘው አቡ ዋሻ[8] በተባለው ፆማዕት (ዋሻ) ገብተው ጸሎታቸውን በመዝሙር ዜማ ሳይቀር እያደረሱ ቆዩ፡፡
  09)^6 ዓ.ም. በሀገሪቱ በተደረገው የመንግሥት ለውጥ ወቅት በእግዚአብሔር ፈቃድ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ በመኪና ዝዋይ ደሴት ወርደው ወደ አዲስ አበባ አምጥተዋቸዋል:: በዓታቸውም በአቶ ኃይለ ልዑል ሀብተ ዮሐንስ[9] የድሮ አውሮፕላን ማረፊያ ሆኖ ነበር፡፡  ወደ አዲስ አበባ እንደገቡም ሐዋርያዊ ተግባራቸውን ቀጠሉ::
  ሰኔ @፪ ቀን 09)^6 ዓ.ም. በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው በብዙ ምእመናን ፊት ያስተማሩት መሠረታዊ ቃለ ምዕዳን በእውነት የተዋሕዶ እምነት ቅንዓት ላላቸው ክርስቲያኖች ዓላማ የሚያስጨብጥ ነበር፡፡
  በወቅቱ ለተገኙት ለማኅበረ ሥላሴ አባላትና ጠቅላላ ምእመናን የሚከተለውን ቃል አስምተዋል፡፡
 ከእሥር ቤት በልዑል እግዚአብሔር ጽኑ ክንድ ተፈትቼ ስመጣ በዚህች ከተማ የእስልምና ተከታዮች ተጨቆንን ዳኝነት ይታይልን ብለው ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸውን ሰማሁ፡፡ በአጸፋው ደግሞ ካህናትና ምእመናን ይኽንን ለመቃወም በአዲስ አበባ ጎዳና ሰልፍ መውጣታቸውንም አደመጥሁ፡፡ እስላሞቹስ ተጨቆንን ብለው ወጡ፡፡ ክርስቲያኖች ምን ተነካን ብላችሁ ሰላማዊ ሰልፍ ወጣችሁ?! ንጉሠ ነገሥቱ ጳጳሳቱ የእናንተ አልነበሩምን?! እኔ ገብረ ሥላሴ አጥፊ ነህ ተብዬ ወደ ግዞት ለእሥራት ስሄድ ማኅበሩ የሥላሴ እንጂ የገብረ ሥላሴ አይደለም ብላችሁ አንድነታችሁን በማጽናት ተደራጅታችሁ ሥራውን ሳትቀጥሉ ለምን ተበታተናችሁ?! በራሳችሁ ገንዘብ ለራሳችሁ መገልገያ የተገዙት አግዳሚ ወንበሮችስ እንዳይወሰዱ ለምን በሕግ አልጠየቃችሁም?!  አስተማሪዎችስ መናንያን፣ ባሕታውያን ነን የምትሉ አንድ ገብረ ሥላሴ ቢታሰር ተተክታችሁ በጎቹን ለምን አልጠበቃችሁም?! በማለት ሕዝቡን ጠየቁ፡፡
 በመቀጠልም በእውነት መናኞች ብትሆኑ ኑሮ ኢታጥርዩ ለክሙ ወርቀ ወብሩረ ያለውን የጌታን ቃል ታከብሩት ነበር፤ አቀብሎ ሸሸ ባልሆናችሁም ነበር፡፡ አሉ፡፡
በማስከተልም የክርስቲያኖች ሰላማዊ ሰልፍ በከተማ እየተዘዋወሩ የአስፋልት መስክ ማልፋት አይደለም፡፡ አንድነት ኃይል ነው፣ ኃይል አንድነት ነው እንደተባለው ወንጌልን በመስበክ በማኀበር በመደራጀት ታላቅ የኾነ ሐዋርያዊ ድርጅት አቋቁሞ ለአረማውያን ጭምር ቃለ ወንጌልን በማሰማት የክርስቲያንን ቁጥር በማብዛት ነው እንጂ በየከተማው አስፋልት መስክ ማልፋት አይደለም፡፡ አሁንም የተኛችሁ ንቁ! የዘመኑ ድንጋይ እንኳን ሕንፃ በመሆን ወደ ሰማይ እየጠቀሰ ሰማይ ሰማይ እያየ ይገኛል፡፡ እናንተ እስከ መቼ ድረስ ግዕዛን ከሌለው አንሳችሁ መሬት ለመሬት ትንፏቀቃላችሁ?! ብረቱ መንኮራኩር ሆኖ ወደ ጠፈር እየሄደ ነው፡፡ እናንተ ግን ሁልጊዜ ከመሬት ሳትላቀቁ ተበታትናችሁ ልትኖሩ ነው?! ተው ተመለሱ ማኅበራችሁን አጠናክሩ፡፡ እኛ አንድ ከሆንን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም የወንጌል መልእክተኞች በማሰማራት በነፍስም በሥጋ ከባዕዳን ተጽዕኖ ነጻ እንዲወጡ ማድረግ በተቻለን ነበር፡፡ በማለት አስተምረዋል፡፡
   በትምህርቱ የተማረኩ ምእመናን ለሚቀጥለው የክርስቲያን ሰንበት ጉባዔ ለመስማት ስሜታቸው ተቀስቅሷል፡፡ በተባለው ዕለትም መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ ያስተላለፉት መልእክት ከላይ የተጠቀሰው ብቻ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ ጥቂቶቹን መልእክቶች እንደሚከተለው ዘግበናቸዋል፡፡
የተዋሕዶ ሃይማኖት እንድትሰበክ ምእመናን በእምነት በምግባር እንዲጸኑ ለዚህ ተግባር የሚያገለግለን እስከ ሞት ድረስ ተጋድሎ በማድረግ የምናደራጀው ክርስቲያናዊ ሐዋርያዊ ማኅበር ማቋቋም ያስፈልገናል፡፡ እኔም ዓላማዬ ወንጌልን ለማዳረስ መምህራንን በቂ ደሞዝ በመስጠት ጥረት ማድረግ ነው፡፡ ለ 06 ዓመታት የታሠርኩት ለአምልኮተ እግዚአብሔር በመቅናት በደሙ የዋጃቸው ምእመናን በጠንቋዮችና ዛር አንጋሾች እንዲሁም ከልዩ ልዩ አህጉራት ክርስቲያኑን ለማሳት የዘመቱ ቢጽ ሐሳውያን መነሣታቸውን ተመልክቼ ባለቤቱም ስላዘዘኝ ነው እንጂ የሳንቲም ድቃቂ፣ የጨርቅ እላቂ፣ ሹመት ሽልማት ሽቼ እንዳልተነሣሁ ሕሊናየ ይመሰክርልኛል፡፡ መንፈስ ቅዱስም የሚያውቀው ነው፡፡
   እንግዲህ ወንጌል እንድትሰብክ ምእመናን እንዲጠበቁ የምንሻ ከሆነ ወሬውን ጭቅጭቁን ትተን እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመኾን ከዚህ ዓለም ፖለቲካ የራቀ በሥላሴ ስም ጠንካራ የስብከተ ወንጌል ማኅበር አቋቁመን ወደ ሥራ እንሰማራ፡፡ አደራ ጥብቅ ሰማይ ሩቅ እንዲሉ ስለ ተሰቀለው ትንሣኤውን ስለገለጸው ሕያወ ባሕርይ አምላክ ስለ ክርስቶስ ጊዜ ሳያልፍብን ከንዋመ ሐኬት እንንቃ፡፡ በማለት ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ ያስተማሯቸውን ትምህርቶች ሰብከቶች ሙሉን በጽሑፍ መጻፍ ስላልተቻለ በቁንጽል ለጊዜው ለዓይነት የተጻፈው ይበቃናል፡፡
    በሳምንቱ በዚያው በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ጉባኤ ዘርግተው የማኅበረ ሥላሴ የድምፅ ማጉሊያ በጠጉር አስተካካዩ አቶ በቀለ ተድላ በዓት ተቀምጦ ስለነበር እንዲመጣ ተደርጎ ከመቅድመ ተአምር ቀጥሎ ስብከት እንደተለመደው በመምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ ሲጀመር ከቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በተለይም በደብሩ አለቃ በረቀቀ ተንኮል ጉባኤውን የሚያሳዝን ድርጊት ተፈጸመ፡፡ ይኸውም በደብሩ አባ ገብረ ሥላሴ ከመምጣታቸው በፊት ስብከት አይካሄድም ነበር፡፡ እርሳቸው በዐውደ ምሕረቱ መቅድመ ተአምር የእመቤታችንን ማሰማት እንደጀመሩ በድምፅ ማጉሊያ የምእመናንን ሕሊና በመረበሽ ለማሳዘን ማስታወቂያ ይነገር ጀመር፡፡ አንድ ዲያቆን ከውስጥ ስለታዘዘ አልፎ አልፎ በማስታወቂያ የስብከት ሥራውን ማደናቀፍ ጀመረ፡፡ በዚህን ጊዜ መምህር ገብረ ሥላሴ ምእመናን ወደ ንዴትና ሁከት እንዳይሄዱ የማረጋጊያ ትምህርት ሰጡ፡፡
    በመቀጠልም ከውስጥ በቅንኣት መንፈስ ተአምረ ማርያም ማንበብ ሲጀምሩ ሕዝቡ ተንኮላቸውን ተረድቶ ለመቃወም ሲነሳሣ መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ እንዲረጋጋ አድርገው የእመቤታችንን ተአምር ስለሆነ የሚያሰሙት ጸጥ ብለን በትዕግሥት እናድምጥ በማለት አርአያ በመሆን ማድመጥ ቀጠሉ፡፡ ከዚህ በኋላ የተአምር ንባቡ እንደተፈጸመ እስቲ ዓላማችንን ለመነጋገር ከዐውደ ምሕረቱ ትንሽ ራቅ እንበልላቸው ብለው ወደ ማዘጋጃ አፍዛዣ ባለው አቅጣጫ ሄደው ማሳሰቢያ ሰጡና ምእመናን ተወያይተው መፍትሔ ለማፈላለግ የሰላም ቡድን ተቋቁሞ ፓትርያርኩንና አለቃውን ለማነጋገር ወሰኑ፡፡ ምርጫ ተደርጎ የሰላም ጓድ ተብሎ ተቋቋመ፡፡ የደብሩ አለቃ የቀድሞው ጸባቴ በጽሐ ጌታሁን ነበሩ፡፡
   ዝርዝር ሁኔታውን ለጊዜው እንተወውና በሚቀጥለው ሳምንት እንኳን ሰባኪው ሕዝቡም እንዳይገባ  የቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ በአለቃው ትእዛዝ እንዲቆለፍ ተደረገ፡፡ ጊዜው ደርግ ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም  በማለት እንቅስቃሴ ላይ የነበረበት ነበር፡፡  ደርግ ዓላማዬን የሚቃወሙ የአድኅሮት  ኃይላት አሉ በማለት ቅስቀሳ የሚደርግበት ወቅት ነበር፡፡
  በዚህ ጊዜ መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ በእሳት አደጋ ፊት ለፊት ካለው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ውጭ ካለው አንድ ዛፍ አጠገብ ምእመናንን ማስተማር ያዙ፡፡
   የደብሩ አለቃ በውጭ የሚሰጠው ትምህርት የፖለቲካ ይዘት ያለው አስመስለው ለአዲስ አበባ የፖሊስ አዛዥ  ስልክ በመደወላቸው ወታደሮችና ፖሊሶች ወደ ጉባኤው ይመጣሉ፡፡
   አባ ገብረ ሥላሴ እንደ ቀድሞው ጊዜ ተቃውሞው የመጣው ከመንግሥት መስሏቸው በኃይለ ቃል መገሠጽ እንደ ጀመሩ ጉዳዩ ከገባቸው ምእመናን አንዱ ሄዶ በትሕትና ዝም ያሰኛቸዋል፡፡ ሌሎች ምእመናን ደግሞ ለመጡት ፖሊሶች የችግሩን መንሥኤ ይነገሯቸዋል፡፡
   ፖሊሶቹም ከደብሩ አስተዳደር የኢትጵያን ትቅደም ዓላማ ለማደናቀፍ አድኃርያን ተሰብስበዋል፡፡ ተብሎ  ለፖሊስ አዛዡ ለኮሎኔል ያደቴ ጉርሙ ተደወሎላቸው እንደመጡ በመናገር  ውስጠ ተንኮሉን ይገልጻሉ፡፡ ከዚያም ምእመናን አባ ገብረ ሥላሴን በታክሲ አሳፍረው  ወደ በዓታቸው ወደ አቶ ኃይለ ልዑል ሀብተ ዮሐንስ ዘንድ እንዲሄዱ በመደረጉ ሁከት ሳይነሣ ቀርቷል፡፡
   የሰላም ጓዱ መምህር ገብረ ሥላሴን ከአለቃው ከጸባቴ በጽሐ ጌታሁን ጋር ለማነጋገር ጥረት አደረገ፡፡ አለቃው ግን ፓትርያርኩ አባ ገብረ ሥላሴን እንዳያስተምሩ መመሪያ ሰጥተውኛል፡፡ ፓትርያርኩን አነጋግራችሁ በእርሳቸው ፈቃድ እንዲያስተምሩ ቢደረግ መልካም ነው አሉ፡፡ በወቅቱ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ናቸው፡፡
    ምንም እንኳን መምህር ገብረ ሥላሴ ከቀድሞው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የማስተማሪያ ፈቃድ ቢኖራቸውም በሰላም ጓዶች ልመና መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሄደው ታዛቢዎች ባሉበት ከፓትርያርኩ ፈቃድ ቢጠይቁም ሊሰጣቸው አልቻለም፡፡
   ከዚህ በኋላ ሕዝበ ክርስቲያኑን ፈቃዳችሁን ለመፈጸም ጠይቄአለሁ፡፡ አሁን ግን ወንጌል እንዳስተምር ያዘዘኝን የፈጣሪዬን ድምፅ እንጂ ሌላ ቃል መስማት አይቻለኝም፡፡ እስከ ሞት ድረስ ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖት ስለወንጌል ዓላማ ተጋድሎ አድርጋለሁ፡፡ በማለት የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል ሲከበር ያለምንም ፍርሃት በዐውደ ምሕረት ተገኝተው አስተምረዋል፡፡
  ሕዝበ ክርስቲያኑ ወደ የቤታቸው ከተመለሱ በኋላ አለቃው ጸባቴ በጽሐ ጌታሁን እንደ ተለመደው ከፓትርያርኩ ጋር በመነጋገር ለሻምበል ጥላሁን ተነግሮ በፖሊስ አስይዘው ቀድሞ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ (በኋላ ግን ማዕከላዊ) ወደ ተባለው እሥር ቤት አስወስደዋቸው በሲሚንቶ ቤት በፖሊስ ዱላ እንደ እባብ አናት አናታቸውን አስቀጥቅጠዋቸዋል፡፡ በዚኽም  ከአፍ ከአፍንጫቸው ደም በብዛት ፈሷል፡፡
   በዚህ ጊዜ ሁሉ ለጠያቂ እንኳን ስንቅ ለማቀበል አስቸጋሪ ነበር፡፡ በኋላ ግን የማኅበረ ሥላሴ አባልና የመምህር ገብረ ሥላሴ ተከታይ የነበሩት ፀጉር አስተካካዩ አቶ በቀለ ተድላ ሻምበል ጥላሁንን ለምነው ስንቅ እንዲገባላቸው በርቀትም ወዳጆቻቸውን እንዲያነጋግሩ አስፈቅደዋል፡፡
    መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ ከእሥር ቤት ከወጡም በኋላ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እየተዘዋወሩ ማስተማራቸውን ቀጠሉ፡፡ ፓትርያርኩና ደጋፊዎቻቸው በተለይም ከሃይማኖተ አበው ኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር የመማክርት አባለት በድምፅ ማጉሊያ ሳይቀር እየተዘዋወሩ የስም ማጥፋት ቅስቀሳ  ያካሄዱ ነበር፡፡
    በመጨረሻም በቂም በቀልና በቅንዓት በመነሣሣት ፓትርያርኩ ከሲኖዶስ ፈቃድ ውጭ በየቤተ ክርስቲያኑ በአባ ገብረ ሥላሴንና በደጋፊዎቻቸው ላይ የግዝት ደብዳቤ አስተላለፉ፡፡
    መምህር ገብረ ሥላሴ ግን ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የትግራይ ሊቀ ጳጳሳት ተጠባባቂ ፓትርያርክ ሆነው ሲኖዶሱን በሚመሩበት ወቅት ለሲኖዶስ አመልክተው በግል ጥላቻና በቂም በቀል የተፈጸመ ግዝት ስለሆነ ግዝቱ በሲኖዶስ ውሳኔ  እንዲነሣላቸው አድርገዋል፡፡
  መምህር ገብረ ሥላሴ ሐዋርያዊ ተግባራቸውን ቀጥለው በማስተማር ላይ እያሉ በብርቱ ታመው የካቲት 0፪ ሆስፒታል[10] ገብተው ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸው ድነዋል፡፡
  ግንቦት 0፪ ቀን  09)8 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ገዳም በአስተማሩት ትምህርትና በገሠጹት ተግሣጽ ወታደራዊ መንግሥትን (የደርግ አስተዳደርን) ዘልፈሃል፡፡ ተብለው ተከሰው እስከ ታኅሣሥ ወር ለሰባት ወራት ታሥረው በፍርድ ቤት ትእዛዝ በነጻ እንዲለቀቁ ተደርጓል፡፡ የታሠሩትም ፍቼ ከሚገኘው ወህኒ ቤት ነበር፡፡
  09)9 ዓ.ም.  ከደቀ መዛሙርት መካከል የማኅበረ ሥላሴ አባል የነበሩት ፀጉር አስተካካዩ አቶ በቀለ ተድላ በበዓለ ገና (በጌታ ልደት) ፍቼ ድረስ በመሄድ ጠይቀዋቸዋል፡፡  
  ዘለፋ ተብሎ የተከሰሱበት ምክንያትም የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ፍልስፍና እግዚአብሔር የለም፡፡ የሚል ስለነበር ይኽንን ርእዮተ ዓለም በማውገዝ ያለ ፍርሃት በታላቁ ገዳም ከመላው ኢትዮጵያ በዓል ለማክበር ለመጡ ምእመናን በማስተማራቸውና ማስጠንቀቂያ በመስጠታቸው ነበር፡፡
   ክሱ የአብዮቱ ደጋፊዎች ነን ባዮች የለውጥ አራማጅ ካድሬዎች የተፈጸመ መኾኑን ያወቁ ውስጠ ክርስቲያን የሆኑት ዳኞች እውነታውን ተረድተው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነጻ እንዲወጡ አድርገዋቸዋል፡፡
    09)&.. በብፁዕ  ወቅዱስ  አቡነ  ተክለ  ሃይማኖት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መልካም ፈቃድ ከአምስት መቶ በሚበልጡ ባሕታውያን[11] ሰባክያነ ወንጌል የባሕታውያን ፍቅር ወሰላም የአንድነት ማኅበር ተቋቁሞ ነበር፡፡ የባሕታውያኑና የሰባክያነ ወንጌሉ ተወካዮች የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሚስፋፋበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ጋር ተወያይተው ነበር፡፡ መምህር ገብረ ሥላሴም በብሕትውናቸውና በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ይታወቁ ስለነበር በቅዱስነታቸው በተመራው ጉባኤ ላይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡






ሥዕለ ገጽ 6 መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በተመራው የባሕታውያን ጉባኤ በተገኙበት ወቅት


 ሥዕለ ገጽ 7 መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በተካሄደው ጉባኤ በባሕታውያንና በሰባክያነ ወንጌል ጉባኤ ላይ በተገኙበት ወቅት
   እንደገናም የጥንት የልጅነት ዘመን ሕመማቸው ተነሥቶባቸው ከወገባቸው በታች በድን ስላደረጋቸው ተስፋ ሳይቆርጡ  ወንጌልን በይፋ ለመመስከር አባ ዘሚካኤል በሚባሉ አንድ መነኩሴ አማካይነት በሸክም ከደብረ ሊባኖስ አዲስ አበባ መጥተው ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ኮሚኒስቶች የጻፉትን  አልቦ እግዚአብሔር የሚል መጽሐፍ በመረጃነት ይዘው ከሃድያን እግዚአብሔር የለም ብለው በአምላክ ላይ ተነሳሥተዋል፡፡ እልም ይላሉ፡፡ በሃይማኖታችሁ ጽኑ  በማለት ለምእመናን አስተምረዋል፡፡
  በዚያን ዕለትም ከከፍተኛ አንድ ቀበሌ 08 የአብዮት ጠባቂዎች መጥተው መነኵሴው አባ ዘሚካኤል እንዲሸከሟቸው በማድረግ ለምርመራ ወስደዋቸዋል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ ተከትሎ ሲሄድ በአብዮት ጠባቂዎችና በፖሊሶች ይታገድ ነበር፡፡ ተክለ ማርያም የሚባል አታክልት እየሸጠ የሚተዳደር አንድ ወጣት ነጋዴ ከሃይማኖት አባታችን አልለይም በማለት ደብደባውን ችሎ ከአብዮት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ተገኝቷል፡፡
  መምህር ገብረ ሥላሴ ለተጠየቁት ጥያቄ የኮሚኒስቶችን የክህደት መጽሐፍ በእጃቸው ይዘው ስለነበር እያሳዩ በይፋ ያለ ፍርሃት መርማሪዎቻቸውን ገሥፀዋል፡፡ ከዋናው ጌታችሁ  ከመንግሥቱ  ኃይለማርያም  ዘንድ አቅርቡኝ አውግዤ ሰማዕትነት እቀበላለሁ፡፡  ወይም  ጎበዞች  ከኾናችሁ ግንባሬን በጥይት ብላችሁ ዕረፍት ላግኝ፡፡ ብለዋል፡፡ ይኽ ሁኔታ ሲሰማ በወቅቱ የወጣቶችና ጎልማሶች አጠቃላይ የስብከተ ወንጌል ማኅበር (አጠቃላይ ጉባኤ)[12] በጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ብዙ ሕዝበ ክርስቲያንና ሊቃውንት በተሰበሰቡበት በአባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ላይ የተፈጸመውን እንግልት በተቃውሞ አሰምቷል፡፡
  ወዲያው መነኵሴው አባ ዘሚካኤል ተሸክመዋቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ውጭ ባለ ዝናብ ከሚያስገባ አንድ መቃብር ቤት  ጥለዋቸው ሄደዋል፡፡
  የአጠቃላይ ጉባኤ ወጣቶች ይኸንኑ ሰምተው በቦታው በመገኘት ጣሪያውን በመክደን፣ ቤቱን አጽድተው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በውስጥ ለጥፈውና አልጋ አዘጋጅተው እንክብካቤ አድርገውላቸዋል፡፡
  ከደብረ ሊባኖስ ድረስ ተሸክመው ያመጧቸው መነኩሴም ከዚያው እያስታመሙ ቆይተው በኋላ ከደብረ ሊባኖስ የኋላ እሸት ከበደ የተሰኘ አንድ መንፈሳዊ ተማሪ በገዛ ፈቃዱ መጥቶ በእርድና ሲያገለግላቸው ቆይቷል፡፡ እርሱም ዛሬ በአንድ ገዳም በተባሕትዎ ጸንቶ በትሩፋት የሚገኝ መናኝ ኹኗል፡፡ በእርሱ ምትክ በውጭ ሲጠይቃቸው የነበረው ተክለ ማርያም ረድእ ሆኖ እስከ ፍጻሜ ሕይወታቸው አገልግሎ ከእርሳቸው  በኋላ ዐርፎ ሥርዓተ ቀብሩ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተከናውኗል፡፡
  ወደ ተነሣንበት ታሪክ ስንመለስ መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ ወንጌልን ለማስተማር ካላቸው ቁርጠኝነት የተነሣ እንደ ቶማስ ዘመርአስ[13] ከቻላችሁ በቅርጫት ጭናችሁኝ ዙሬ ልመስክር፡፡ በማለት ለምእመናንና ለመንፈሳውያን ወጣቶች ስላሳሰቡ የምትገፋ ብስክሌት ምእመናን ገዝተውላቸው በብስክሌት እየተገፉ ደብረ ሰላም ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ጥቅምት @፯ ቀን ተገኝተው አስተምረው ሲመለሱ ከመኪና ጋር ተጋጭው ወድቀው ስለተሰበሩ ዳግማዊ ምኒልክ ገብተው ዘጠኝ ወር ሙሉ  ሲታከሙ ቆይተው ወጥተዋል፡፡ በሆስፒታልም ለሐኪሞችና ቆስለው ለሚመጡ ወታደሮች ሳይቀር ቃለ እግዚአብሔር ከማሰማት የተቆጠቡበት ዕለት አልነበረም
   በዚህም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ ሆስፒታል ገብተው ታክመው ወጥተዋል፡፡ ዳሩ ግን ሕመማቸው እየበረታ ሄዶ አሁንም ከፍተኛ ሕመም ሲታመሙ ቆይተው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ገብተው በቀዶ ጥገና (Surgical operation) እንደ ድንጋይ የተጋገረ በሽታ ወጥቶላቸዋል፡፡ በዚህም ሕይወታቸው ከሞት ተርፎ በፓትርያርኩ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፈቃድ በመንበረ ፓትርያርኩ ግቢ ቦታ ተፈቅዶላቸው በሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ የግል ገንዘብ ቤት ተሠርቶላቸው ማረፊያ አግኝተዋል፡፡ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ  የሕክምና ወጪና ሠርከ ኀብስት በመቻል ይረዷቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡


ሥዕለ ገጽ 8 ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ
   ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም በየወሩ ለመምህር ገብረ ሥላሴ እርዳታ ያደረጉላቸው ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ ወደ ደብረ ሊባኖስ ለመሄድ የተገለጸላቸው የጸድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጥሪ ስለነበር እግረ መንገዳቸውንም የክህደትን አራማጆች ለማውገዝ ቁርጥ ሐሳብ አድርገው ለፓትርያርኩ በፈሊጥ  እንዲነገር ተደርጎ በደብረ ሊባኖስ ገዳም በቅዱስነታቸው ፈቃድ በተሰጣቸው ቤት ሲታመሙ ቆይተው በጠቅላላው 0፫ ዓመት ካልጋ ሳይለዩ ጸሎት፣ ተግሣጽና ማስተማር ከአንደበታቸው ሳይቋረጥ ኖረው በዚህ ዓለም ለአባቶቻቸው ለሐዋርያት የተሰጠው ልዩ ልዩ ዕድል ለእርሳቸው ምንም ሳይጎድል ተሰጥቷቸው ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያነታቸው አርአያ የሚሆን፣ ለምእመናን ድኀነት፣ ፈውስ፣ በረከት የሚያሰጥ ሐዋርያነታቸውን ፈጽመው መጋቢት @9 ቀን  09)* ዓ.ም.  ዐርፈው በደብረ ሊባኖስ ገዳም በቤተልሔም ጓሮ እነ አባ ጴጥሮስ ኡሉሉ እና መናኙ አለቃ ተክለ ጽዮን  ባረፉበት አጠገብ ሥጋቸው አንቀላፋቷል፡፡
   በደብረ ሊባኖስም ለመጨረሻ ጊዜ እንደ አባቴ እንደ አቡነ ጴጥሮስ ብለው ያወገዙት ግዝትም ሥራ ሠርቶ እግዚአብሔር አልባ መንግሥታትን አናውጾ አምላካዊ ኃይል ተገልጧል፡፡ ከዚህ በላይ በምስጢር የተከናወነ ብዙ ነገር አለና ሁሉን ለመግለጽ ለጊዜው አልተቻለም፡፡ ለዝክረ ነገር እግዚአብሔር በበረሐ ስንዴ እንደሚዘራላቸው፣ ድካማቸው ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር፣ በመጨረሻም ቅዱስ ጴጥሮስ ከሮም መጥቶ አክሊል ሲያቀዳጃቸው እርሳቸውም ከማረፋቸው በፊት አይተዋል፡፡
   በወንጌል ተጋድሎ አጋራቸው የነበሩትም ባሕታዊ ገብረ ጊዮርጊስ ትኩነህ ተገልጾላቸው ለምሥጢር ተካፋይ ደቀ መዛሙርት መንገራቸው ይታወቃል፡፡ ይቆየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡
ተፈጸመ


[1]  በራዕየ ዮሐንስ የተጠቀሰውን አንሥተው ነው፡፡
[2] በሬዎች ማለታቸው ነው፡፡
[3]  ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ካልአይ ሊቀ ጳጳስ በ 08)፹፯ ዓ.ም. ተወልደው በ09)፹፫ ዓ.ም. ነሐሴ 0፪ ቀን ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ ዐርፈው ሥርዓተ ቀብራቸውም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ቆሞሳት፣ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት መቐሌ በሚገኘው ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል  ተፈጽሟል፡፡

[4]   ጸባቴ በጽሐ ጌታሁን መስከረም 06 ቀን  09)8 ዓ.ም.  አቡነ ባስልዮስ ተብለው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከተሾሙት ሦስት ኤጲስ ቆጶሳት አንዱ ነበሩ፡፡
[5] የዝዋይ (የዛይ) ሐይቅ ከአዲስ አበባ ሐዋሳ በሚወስደው መንገድ አንድ መቶ ስድሳ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በሐይቁ ውስጥ አምስት ደስያት(ደሴቶች) ይገኛሉ፡፡ አባ ገብረ ሥላሴ የተጋዙት በአርሲ ሀገረ ስብከት ሥር ወደ ሚገኘው ደብረ ጽዮን ደሴት ነበር፡፡ የዛይ ደስያት በመካከለኛ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ዘመን የተጠናከረ የቤተ ክርስቲያን የትምህርት ማዕከል፣ የተደራጀ ገዳማዊ ሕይወት የነበረባቸው፣ የተለያዩ ቅዱሳን አበው በግዞት የተቀመጡባቸው፣ የሚማሩባቸውና የቅዱሳት መጻሕፍት ማዕከላት ነበሩ፡፡ ለአብነትም በአጼ ሰይፈ አርእድና በአጼ ዓምደ ጽዮን ዘመናት አባ አሮን ዘመቄት' አባ በጸሎተ ሚካኤል' አባ አኖሬዎስና እጨጌ አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ ወደ ዛይ ደስያት ተግዘው ነበር(ገድለ አቡነ ፊልጶስ (09)(9: )7፣ Taddesse 1972)፡፡ በምሥራቅ ሸዋ አካባቢ የተወለዱትና በምሥራቅ ጎጃም መርጡለ ማርያም አካካቢ የሚገኘውን የደብረ ጽሙና ገዳምን የመሠረቱት አባ ሲኖዳ ከሕጻንነታቸው ጀምሮ የተማሩት' ያደጉትና የመነኮሱት በዛይ በሚገኙ ደስያት ነበር፡፡
[6]   ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ካልአይ ከ09) ዓ.ም. እስከ 09)*፬ ዓ.ም. የነበሩ ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡
[7]  በኋላ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ በመባል የሚታወቁት አባት ናቸው፡፡ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲሁም የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ ሲሆኑ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል መምሪያ ሥራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ በ09)(6 ዓ.ም. ትምህርት ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት በሚል ርዕስ ያዘጋጁ፣ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ በምክር አገልግሎታቸውና በትሩፋታቸው የሚታወቁ አባት ነበሩ፡፡ ከአባ ገብረ ሥላሴ ጋር ያቆራኛቸውም ለስብከተ ወንጌል የነበራቸው ፍቅር ነው፡፡
[8]  ይኽ ዋሻ ዛሬም የአባ ገብረ ሥላሴ ዋሻ ተብሎ የሚጠራ ሲኾን ዙሪያው በቅንጭብና በሐረግ በመሸፈኑ ውስጡን ገብቶ ለማየት ያስቸግራል፡፡
[9]  አቶ ኃይለ ልዑል የማኅበረ ሥላሴ ጸሐፊ ነበሩ፡፡
[10]  ስድስት  ኪሎ ከሰማዕታት ሐውልት ጎን ከሚገኘውና በቀድሞ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታል 
[11] ከአባ መሸ በከንቱ ጋር በ09)(3ዓ.ም. በደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን በተደረገ ቃለ ምልልስ የተገኘ መረጃ ነው፡፡
[12] በዘመነ ደርግ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በቤተ ክርስቲያን ላይ ይደርስ በነበረው ተጸእኖ ከአዲስ አበባና ከተለያዩ አኅጉረ ስብከት በመንፈሳዊ ቅንአት የተሰባሰቡ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት የወጣቶችና ጎልማሶች አጠቃላይ የስብከተ ወንጌል ማኅበርን(አጠቃላይ ጉባኤን) መሥርተው ነበር፡፡ ይኽ ጉባኤ በደርግ ትእዛዝ እስኪበተን ድረስ በየአሥራ አምስት ቀን እሑድ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤቶች በየተራ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ያካሂዱ ነበር፡፡ ይኽ ጉባኤ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት አደባባይ ወጥተው ሀልዎተ እግዚአብሔርን፣ የሃይማኖትን ታላቅነትና የመስቀልን ክብር እንዲመሰክሩ በማደረግ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የማይዘነጋ ቦታ ይዟል፡፡
[13] ቶማስ ዘመርአስ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዳይተጋ እግሮቹን ቢቆረጥም ደቀ መዛሙርቱ በቅርጫት ውስጥ አስቀምጠውት በአህዮች ላይ ጭነውት  እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር፡፡ ይኽንን አገልግሎቱን ለማስቆም የአህዮቹን ራስ ቢቆርጡበት በተአምር የአህዮቹን አንገት ከቦታው በመመለስ የወንጌል አገልግሎቱን ቀጥሏል፡፡ አባ ገብረ ሥላሴ ይኽንን የተናገሩት የእርሱን ፈለግ ለመከተል አስበው ነው፡፡