የአጤ
ዋሻ ቅድስት ማርያም አጭር የታሪክ ቅኝት
በመምህር ሰሎሞን ወንድሙ መታፈሪያ
ሀገራችን በርካታ ምዕተ ዓመታትን ያስቆጠሩ ድንቅዬ የታሪክ መስህቦች አሏት፡፡
የቀደሙት አበው ዘመናዊ ሥልጣኔ ባልነበረበት ዘመን ሀገር በቀል ሥልጣኔያቸውንና ጥበባቸውን ተጠቅመው በጣም የሚያስደንቁ አያሌ ገዳማትን
ገድመዋል፣ አድባራትን ደብረዋል፡፡
በተለያዩ ቅዱሳት መካናት የምናገኛቸው ንዋያተ ቅዱሳት፣ በተለያዩ ዘመናት
የታነጹ አብያተ ክርስቲያን በተደሞ ላስተዋላቸው፣ ቀርቦ ለሚፈትሻቸው የሚገልጹት ጥልቅ ምስጢር፣ የሚያወጉት ድንቅ ታሪክ አላቸው፡፡
በርካታ ምዕተ ዓመታትን የኋልዮሽ ተጉዘው በጉያቸው ሸሽገው ያኖሩትን ሀብታቸውን በቋንቋቸው ስለሚገልጹ ገላጭ አያሻቸውም፡፡
በዘመናችን የታሪክ ማኅደር፣ የጥበብና የሥልጣኔ ምድር፣ የአምልኮት የዕውቀት
ምድር የሆኑ ገዳማትና አድባራት በዘመን ብዛት በእድሳትን እንክብካቤ ማጣት ሲቦዳደሱ ማየትና መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ
ሁኔታ ከቀጠለ ስለመካናቱ ለማወቅ ቦታዎቹን ከማየት ይልቅ ወደ አብያተ መጻሕፍት መሔድ ሳይቀል አይቀርም፡፡ በእጃችን የያዝነው ሳያመልጠን
የጨበጥነው ሳይፈተልክብን ተገቢውን ትኩረት ልንሰጥ ይገባናል፡፡
ሀገራችን በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት ጸንታ ለመኖሯ ዛሬ የምናያቸው መንፈሳዊና
ቁሳዊ ቅርሶቻችን፣ ትውፊታዊ የአኗኗር ዘይቤያችን ከምንም በላይ የዕድሜ ባዕለ ጸጋ ቅዱሳት የአምልኮ ሥፍራዎቻችን ሕያዋን ምስክሮች
ናቸው፡፡ የአጤ ዋሻ ቅድሳት ማርያም ጥንታዊ ታሪክ ሸሽጋ የያዘች፣ ክርስቲናዊ ትውፊት ጠብቃ የቆየች የቅርስ ባለ አደራ የትውፊት
ሙዳይ ናት፡፡
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ከአዲስ አበባ ፻፳፫ ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው
የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ከጎሼ ባዶ የገጠር ከተማ አካባቢ የምትገኘው ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
በደብረ ብርሃን ከተማ መግቢያ ላይ የምትገኘው የጤባሴ ከተማ ሲደርስ በስተግራ
በኩል ያለውን ወደ ጅሁር የሚወስደውን የጠጠር መንገድ ይዞ ጥቂት እንደተሔደ በድጋሚ በስተቀኝ በኩል ያለውን መንገድ ይዞ ወደ ጎሼ
ባዶ ከተማ ዐሥር ኪሎ ሜትር መጓዝ ያስፈልጋል፡፡
ወደ አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለመድረስ ሁለት አማራጮች አሉ፡፡
የመጀመሪያው ወደ ጎሼ ባዶ ከተማ ሰባት ኪሎ ሜትር እንደተጓዙ ቀጣኒት
ሲደርሱ በስተግራ የተከለለውን አቅጣጫ ጠቋሚ ቀስት ተከትሎ ከመንገዱ በስተግራ በኩል ያለውን የእግር መንገድ ይዞ ቁልቁለቱን እያንደረደረ
ይወስዳል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ጎሼ ባዶ ቀበሌ ገበሬ ማኅበርን መንገድ ይዘው ሜዳ ሜዳውን
የሚወስደው መንገድ ነው፡፡ የመጀመሪያው መንገድ ቁልቁለትና አጭር በመሆኑ ተመራጭነት ሲኖረው ሁለተኛው ደግሞ ረጅምና ሜዳማ በመሆኑ
ለአረጋውያን አመቺ ነው፡፡
ቂጣለኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያምን ቤተ ክርስቲያን ሰበካ
ጉባኤ ሥር የሚተዳደር ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የአካባቢው ምእመናን በቦታው ርቀት በየቀኑ አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያምን ቤተ ክርስቲያን
መመላለስ ባለመቻላቸው በቅርባቸው መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ጽሌው ከአጤ ዋሻ ሔዶ የተተከለ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የደስታ
ተክለ ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ቂጣለኝን «የቀበሌ ስም በላይኝው ወግዳ ካጤ ዋሻ በስተቀኝ ያለ ቀበሌ፡፡» በማለት ይገልጸዋል፡፡
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በስተግራ በሚታየው ጉብታ ላይ ደግሞ የቅዱስ
እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ከዐሥር ዓመታት በፊት ካህናት በመሰላል እየወጡና እየወረዱ የሚያገለግሉበት ዋሻ ውስጥ ነበረ፡፡ አሁን
ግን ሕዝቡ ከዋሻው ግርጌ ቤተ ክርስቲያን እንዲተከልለት በመጠየቁ መቃኞ ተሠርቶለት መንፈሳዊ አገልግሎት እያገኘ ነው፡፡
የመመለሻው ነገር እንጂ ወደ አጤ ዋሻ ለመውረድ እንኳን ቀላል ነው፡፡
መንገዱ ራሱ እያስፈገገ፣ አንዳንዴም እያስጨፈገገ ወደ ቤተ ክርስቲያን ያደርሳል፡፡ ዛሬ የአጥቢያውንና የአጎራባች ቀበሌዎች ምእመናን
ምስጋና ይድረሳቸውና በየጊዜው መንገዱን ባይሠሩትና ባያሳጥሩት ኖሮ የቁልቁለቱ መንገድ ዕረፍት እንድናደርግ ይጠይቀን ነበር፡፡ ፊታችንን
ወደ ደቡብ መልሰን ከሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ስንጓዝ እየተደንደረደርንና እየተሸቀነጠርን ከመጨረሻው ሜዳ ላይ ስንደርስ ከኮረብታ ሥር
የሚመነጭ ውሃ እናገኛለን፡፡ በአጠገቡ ደግሞ ከትልቅ የሾላ ዛፍ ሥር የሚመነጭ ጠበል እናገኛለን፡፡ ይኽ ሥፍራ በጣም ደስ የሚያሰኝ
ማራኪ ልምላሜ የሚታይበት፣ ለጥምቀትና ለሌሎች ክብረ በዓላት ሥርዓተ ንግሥ የሚከናወንበት መስክ ይገኛል፡፡ ወደ ደቡብ ስንዞር ደግሞ
የዕድሜና የታሪክ ባዕለ ጸጋዋ የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ግርማ ከኮረብታው ግርጌ ተመቻችታ ተቀምጣለች፡፡
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ዙሪያ ገባዋ በኮረብታ የታጠረ ሲሆን ቀና
ሲሉ ከሰማይ በቀር ምንም የሚታይባት ከመሬት በታች ያለች ሌላ መሬት ነች፡፡ ከየኮረብታው ሥር የሚፈልቁት ምንጮች የአጤ ዋሻን በውሃ
ላይ የተመሠረተች አስመስሏታል፡፡ አካባቢውን ለመጠበቅ አጥር አያሻም፡፡ በዙሪያዋ ያሉትን መውጫዎች መጠበቅ ብቻ በቂ ነው፡፡ የተቀረው
የማይታሰብ ሕልም ነው፡፡
አጤ ዋሻ የምድር ዳርቻ ድንበር፣የምድር መሠረት፣ ማዕከለ ምድር መስላ በመታየት
የሌላውን ሥፍራ ሕልውና ታዘናጋለች፡፡
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት በተመለከተ
በጹሑፍ የተደገፈ ማስረጃ ባይኖርም የተተከለችበትን ዘመን የሚጠቁ መረጃዎች ግን አሉ፡፡ መረጃዎቹ በትክክል በማንና መቼ እንደተተከለች
የመግለጽ ዓቅም ባይኖራቸውም ጥንታዊነቷን ግን በሚገባ ለማስረዳት ብቃት አላቸው፡፡
የአጤ ዋሻን የት መጣ ስንዳስስ በመጀመሪያ መረጃነት የምንጠቀሰው በ፲፱፻፺፪
ዓ.ም. በተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት የታተመውን የተአምረ ማርያም መጽሐፍ ነው፡፡ በመጽሐፉ ፻፲፪ኛው ተአምር በገጽ ፬፻፯ እንዲኹም
በባለ ፬፻፪ ተአምር መጽሐፍ ውስጥ ተአምር ፵፪ ላይ የተጻፈው ዓረፍተ ነገር እንዲህ ይላል «አጤ ዋሻ ለእመቤታችን በብፅዓትነት የተሰጠች ቦታ ነች፡፡ ይኸችውም ከኢየሩሳሌም የመጡ የአክሱም ካህናት ርስት የሆነች
ከወግዳ ምድር አጤ ዋሻ ናት፡፡» ይኽን ተአምር በመነሻነት ከወሰድን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደው ልጇ ጋር
ገዳማተ ቅብጥን ለመባረክ፣ የሰማዕታትን ስደት ለመባረክ ወደ ምድረ ቅብጥ ከተሰደደች በኋላ ገዳማተ ኢትዮጵያንም ለመባረክ ወደ ሀገራችን
እንደመጣች የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ያስረዳል፡፡ በዚኽን ጊዜ እመቤታችን ከልጇ ጋር ካረፈችባቸው ቅዱሳት መካናት አንዷ አጤ
ዋሻ ቅድስት ማርያም ናት፡፡ ይኽ የታሪክ ምስክርነት በድርሳነ ዑራኤል የታኅሣስ ወር ገጽ ፶፩ ቁጥር ፵፬ ላይም ተጽፎ ይገኛል፡፡
ይኽን መነሻነት ከያዝን በአጤ ዋሻ ማርያም ቅድስት ማርያም ያሉት አረጋውያን አበው እንደሚያስረዱንም ቦታዋ መሥዋዕት ኦሪት ሲሠዋባቸው
ከነበሩት ቅዱሳት መካናት አንዷ እንደነበረች እናረጋግጣለን፡፡
የደስታ ተክለ ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ቂጣ አለኝ የተባለውን ቦታ አንጻራዊ መገኛ ሲገልጽ ቂጣ አለኝ የቀበሌ ስም በላይኛው ወግዳ ካጤ ዋሻ በስተቀኝ ያለ
ቀበሌ በማለት ገልጾታል፡፡ ይኽም
በተአምረ ማርያም በወግዳ ምድር ያለችው አጤ ዋሻ ሌላ ሳትሆን ይኽችው በሰሜን ሸዋ ያለችው መሆኗን ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡
ሌላኛው የታሪክ ገጽታ ደግሞ የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ
ክርስቲያን ዕድሜ ከአንድ ሺህ አንድ መቶ ዓርባ ስምንት ዓመታት በላይ እንደሆነ ይገልጽልናል፡፡ ለዚህ ገለጻ መነሻ የሚሆነው ታሪክ
ከታቦተ ጽዮን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ዮዲት ጉዲት አኵስም ጽዮንን ለማቃጠል ሠራዊቷን አስከትላ ስትዘምት ካህናተ አኵስም ታቦተ ጽዮንን
ይዘው ሲሸሹ በሸዋ አርፈዋል፡፡
ብዙ የታሪክ ጸሐፍት ይኽንን እውነታ ቢጋሩትም አብዛኛዎቹ ዛሬ መርሐ ቤቴ የሚባለውን
አካባቢ ከመጥቀሳቸው በስተቀር በትክክል የተቀመጠችበትን ሥፍራ አልገለጹም፡፡
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ካህናት በቃል እንደሚተርኩትና ለቅርስ
ጥበቃ ባላቸው አነስተኛ ግንዛቤ ያጠፉትን ዛሬም በመጥፉት ዋዜማ ላይ የሚገኙት ጥንታዊ ቅርሶች እንደሚያስረዱት ታቦተ ጽዮን በስደት ወደ ዛሬው የምሥራቅ ሸዋው ዟይ ደሴት ሔዳ በስሟ
ደብረ ጽዮን ተብሎ በተሰየመው ደሴት ላይ ለ፵ ዓመታት ከመቀመጧ አስቀድሞ የዮዲት ሠራዊት ወደ አካባቢው እስኪመጣ ድረስ በአጤ ዋሻ
ማርያም ተቀምጣ ነበር፡፡ ይላሉ፡፡
በተጨማሪም በተአምረ ማርያም ከአባትሽ ከዳዊት ርስት ከኢየሩሳሌም የመጡ የአኵሱም ካህናት ርስት የሆነችው ከወግዳ ምድር አጤ ዋሻ ናት፡፡ ተብሎ እንደተገለጸው ርስታቸው የሆነችውን አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም በሚገባ ስለሚያውቋት በዚያን
የችግር ዘመን ታቦተ ጽዮንን በሚያውቁት ሥፍራ አምጥተው አስቀምጠዋታል፡፡» ይላሉ፡፡ በዚያን ዘመን ታቦተ ጽዮን ያረፈችበት ዋሻም
የአጤ ዋሻ በማለት እንደተጠራ ይተርካሉ፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የምንመለከታቸው የታሪክ መረጃዎች ከላይ የተጠቀሱትን
ሁለት የታሪክ መረጃዎች መቀበል ለማይሹ ሰዎች የአጤ ዋሻ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዕድሜ ቢያንስ ከግማሽ አምአት በላይ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡
በዕቃ ቤት የሚገኘው የቤተ ክርስቲያኒቱ አርባዕቱ ወንጌል ላይ የተጻፈው ጽሑፍ
በአጼ ዓምደ ጽዮን ልጅ በአጼ ሠይፈ አርዕድ ዘመን (፲፫፻፴፬-፲፫፻፷፬ ዓ.ም.) እንደተጻፈ ያስረዳል፡፡ ይኽ ደግሞ መጽሐፉ ከመጻፉ
አስቀድሞ የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንደነበረች ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን
የዕድሜ ባዕለ ጸጋ ብትሆንም ተገቢውን ትኩረት አላገኘችም ወይንም የታሪክ ተመራማሪዎችንና የጸሐፊዎችን ቀልብ አልሳበችም፡፡
ለአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በስፋት ያለመታወቅ
ሦስት ዐበይት ምክንያቶችን መገመት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ቦታዋ ዙሪያዋን በተራሮች የተከበበችና በተፈለገው ጊዜ ለመሄድ የሚቻልበት
አመቺ መንገድ ባለመኖሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የቦታዋን ታሪክ የሚያስተዋውቅ፣ ወደ ቦታዋ ለሚመጡ እንግዶች
ታሪኳን በአግባቡ በመግለጽ የቦታዋን ክብር የሚያሳይ ሥራ በስፋት ባለ መሠራቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ሦስተኛ ግምት ደግሞ ብዙ ታላላቅ
ገዳማትና አድባራት በብዙ ምእመናን በየዘመኑ የሚጎበኙት ለቦታቸው የተለየ ቃል ኪዳን እንደተሰጠው በመግለጽ ነው፡፡ በአጤ ዋሻ ቅድስት
ማርያም ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ሦስቱም ነገሮች ስላልተሠሩ ቦታዋን የታሪክ ተመራማሪዎችም ይኹኑ ምእመናን በስፋት ሊያውቋት አልቻሉም፡፡
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ለረጅም ዓመታት በዋሻ ውስጥ ስትኖር ቆይታ በአጼ
ይኵኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት ከዋሻው ወጥታ በሣር ክዳን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብታለች፡፡ ለረጅም ዘመናት የቆየችበት ዋሻ መግቢያም
ከበላዩ የነበረው ቋጥኝ ድንጋይ ተደርምሶ ዘግቶታል፡፡ ዛሬ ዋሻውን በርቀት ለማየት ካልሆነ በስተቀር ገብቶ ማየት አይቻልም፡፡
ይኽ ታቦተ ጽዮን በስደት ዘመን የተቀመጠችበት የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም
ዋሻ ዛሬ የዝንጀሮና የአራዊት ማደሪያ ሆኗል፡፡
ስለዚህም
ታቦተ ማርያም የምታርፍበት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በሣር ክዳን ተሠርቷል፡፡ በሣር ክዳን ለተሠራችው ቤተ ክርስቲያን በዳግማዊ ምኒሊክ
ዘመነ መንግሥት ራስ ጎበና ዳጬ በዙሪያዋ ያለውን ቦታ በርስትነት ስለሰጧት የዱቢሳና መቀኝ ተወላጅ የሆኑት አቤቶ ወልዴ ሕዝቡን
አስተባብረው የተሻለ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል፡፡
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ባለውለታ
ናት፡፡ በስደትና በችግር ዘመናት የአኵስም ጽዮን ጽሌና ንዋያተ ቅድሳትን በመሸሸግ ለዛሬ እንዲደርሱ አድርጋለች፡፡
በተጨማሪም በ፲፱፻፳፯ ዓ.ም የኢጣሊያ ሠራዊት ሀገራችንን በወረረበት ወቅት
የአዲስ አበባው የመናገሻ ገነተ ጽኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጽሌ በጠላት እንዳይዘረፍ ቄስ መኩሪያ ወልደ ዮሐንስና አጋፍሪ በየነ ወልደ
ዮሐንስ የተባሉ ካህናት የአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጽሌ ወደ አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም በስውር ወስደው አስቀምጠውት ነበር፡፡ አጤ
ምኒልክ ወደ አድዋ ሲዘምቱ ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስን ይዘው ሄደው እንደ ነበር ይታወቃል፡፡ ስለዚህም ኢጣሊያ በአድዋ ያጣችውን ድል
ለመበቀል ዳግመኛ ለወረራ በመጣችበት ወቅት የአኵስም ሐውልትን በዘረፋ ወደ ሮም እንደወሰደችው፣ በገዳማትና በአድባራት ላይ እሳት
እንደለኮሰችው፣ አባቶችን እንደፈጀችው በጦርነቱ ወቅት ኢትዮጵያውያንን ሲራዳቸው የነበረውን የአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጽሌ ቢያገኘው
ሊያጠፋው እንደሚችል ስጋት የገባቸው አባቶች ለታቦቱ መሸሸጊያ የመረጡት አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያምን ነበር፡፡
የኢጣሊያ
ወራሪ ጦር ከሀገር ሲወጣና ሀገር ሲረጋጋ የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ካህናት ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስን እስከ አዲስ አበባ ድረስ በእግር
ተጉዘው በወታደር አሳጅበው አምጥተው በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በተገኙበት
በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት አስረክበዋል፡፡
የአጤ
ዋሻ ቅድስት ማርያም ካህናት በአድዋ ጦርነት ዘምቶ የነበረውን የአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጽሌ ከጠላት ሰውረው በአደራ በማቆየታቸውና
በመጨረሻም በብዙህ ድካምና መንገላታት አዲስ አበባ ድረስ አምጥተው በማስረከባቸው ከንጉሠ ነገሥቱ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ይኽንን ታሪክ በወቅቱ የአካባቢው የጭቃ ሹም የነበሩትና ጽሌውን በወታደር አሳጅበው
አዲስ አበባ ባመጡት አቶ አፍኔና ሌሎች አረጋውያን ምስክርነት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም የሣር ክዳን ቤተ ክርስቲያን በአጼ ኃይለ
ሥላሴ ዘመን ስለፈረሰ በአባ ጣሴ ገብረ ሥላሴ አሳሳቢነት በእቴጌ መነንና በቀኝ አዝማች ድጋፌ ገብረ ኢየሱስ አማካኝነት ቆርቆሮ፣
ምስማርና መሐንዲስ በመገኘቱ ሕዝቡ በጉልበቱ ተሳትፎ ለማደስ ችሏል፡፡ ደርግ በነገሥታቱ ለቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ተሰጥቶ የነበረውን
ርስት በመውረሱና የሕዝቡም አቅም ደካማ በመሆኑ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ለረጅም ዓመታት ምንም ዓይነት ዕድሳት አላገኘም፡፡
ስለዚህም ግድግዳው ተሰነጣጥቆ ጣራውን የተሸከሙት ምሶሶዎች ለመውደቅ ዘምመው
ዓውደ ምሕረቱ ተፈነቃቅሎ በአስፈሪ ኹኔታ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ይኽ ሁኔታ ያለምንም ዕድሳት ቢቀጥል ኖሮ የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም
ቤተ ክርስቲያንን የምናገኛት በታሪክ መጻሕፍት ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔር ፈቃዱ በመድረሱ ሕንጻው ላይ እየደረሰ
ያለው ችግር ታውቆ ምእመናንን በማስተባበር አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ታንጾ ቅዳሴ ቤት የሚከበርበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡
በአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም በርካታ የብራና መጻሕፍት፣ ታቦተ ጽዮን ትገለገልበት
የነበረው የእንጨት ድንኳን ቅሪቶች፣ በኢጣሊያ የወረራ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት የነበሩት የብጹዕ አቡነ አብርሃም
የእጅ መስቀል፣ ጥንታዊ አልባሳትና ሌሎች ንዋያተ ቅዱሳት ይገኛሉ፡፡ በአጥቢያው በሚገኙ ምእመናን ዘንድም የጸሪቀ መበለት ትውፊት
በስፋት የተለመደ በመኾኑ በሰንበት ቀን እናቶች በአግልግል ዳቤ ቋጥረው ይመጣሉ፡፡ አልፎ አልፎም በአንዳንድ እናቶች ዘንድ የሰንበት
እሳት ትውፊት ሲፈጽም ይታያል፡፡
በአጤ
ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ለክብረ በዓል ሥርዓተ ንግሥ በሚፈጸምበት መስክ የእመቤታችን ጠበል ይገኛል፡፡
በአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እስከ ፲፱፻፹፭ ዓ.ም ድረስ
የቅዳሴው አገልግሎት የሚካሔደው እንደጥንታውያን ገዳማት ከሰንበትና ከበዓለ ሃምሳ በስተቀር ውሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬ በአንዳንድ
ችግሮች የተነሣ የቅዳሴው ሰዓት እንደ ከተማ ከአጽዋማት ቀናት በቀር በጠዋት ሆኗል፡፡ በአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን
በዓቢይ ጾምና በፍልሰታ ለማርያም ሰዓታት ሲቆም በተለያዩ ክብረ በዓላት ደግሞ ማኅሌት ይቆማል፡፡ ጸሎተ ቅዳሴውም በሰንበትና በወርኃዊ
በዓላት አይታጐልም፡፡ በየዓመቱ መስከረም ሃያ አንድ ቀን፣ ጥር ሃያ አንድ ቀን፣ የደብረ ዘይት ዕለትና ግንቦት ሃያ አንድ ቀን
በአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥርዓት በርካታ ምእመናን በተገኙበት በዓለ ንግሥ ይፈጸማል፡፡
በተለይም
በደብረ ዘይት ከአዲስ አበባና ከተለያዩ አካባቢዎች በመሰባሰብ ታላቅ መንፈሳዊ ክብረ በዓል ይደረጋል፡፡