ድንቅ ተአምር በአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም |
ጥንታዊው የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን |
አዲስ የተገነባው ጥንታዊው የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን |
በዚኽ
ቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማን ይችላል? ከእኛስ ወጥቶ ወደ ማን ይሄዳል? ፩ ሳሙኤል ፮ ፡ ፳ ፡፡
ይኽ ጥያቄ የተጠየቀው በቤትሳሚስ ሰዎች ነበር፡፡ እስራኤላውያን በሊቀ ነቢያት ሙሴ
አማካኝነት የተቀበሉት የቃል ኪዳኑ ታቦት በፍልስጤማውያን በምርኮ ተወሰደ፡፡ ለእግዚአብሔር ተገቢውን ክብር ባለመስጠታቸው
ክብራቸው፣ ሞገሳቸውና ድል የምትነሣ ኃይላቸው ታቦተ ጽዮን በጠላቶቻቸው ተወሰደች፡፡ በቤተ መቅደሱ የሚኖሩና እግዚአብሔርን
ሳያውቁ ያገለግሉት የነበሩት የሊቀ ካህናቱ የኤሊ ልጆች ይሠሩ የነበረው ኃጢአት ለቃል ኪዳኑ ታቦት በምርኮ መወሰድ አንድ
ምክንያት ነበር፡፡
የታቦተ ጽዮንን ድንቅ
ተአምር የተመለከቱ ፍልስጤማውያን በመደናገጥ የእስራኤልን አምላክ
ታቦት ስደዱ፡፡ ፩ ሳሙኤል ፭ ፡ ፲፩፡፡ በማለት ታቦተ ጽዮን ወደ
ሀገሯና ወደ ሕዝቧ እንድትመለስ ጠይቀዋል፡፡
በዘመናችንም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ከደብረ ብርሃን ከተማ ዐሥር ኪሎ ሜትር ርቀት
በምትገኘው በአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ተመሳሳይ ታሪክ ተፈጽሟል፡፡ ታሪኩ እንዲኽ ነው፡፡
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት በተመለከተ በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም.
በተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት የታተመው የተአምረ ማርያም መጽሐፍ ፻፲፪ኛው ተአምር በገጽ ፬፻፯ እንዲኹም በባለ ፬፻፪
ተአምር መጽሐፍ ውስጥ ተአምር ፵፪ ላይ የተጻፈው ዓረፍተ ነገር እንዲህ ይላል «አጤ ዋሻ ለእመቤታችን በብፅዓትነት የተሰጠች ቦታ ነች፡፡ ይኸችውም
ከኢየሩሳሌም የመጡ የአክሱም ካህናት ርስት የሆነች ከወግዳ ምድር አጤ ዋሻ ናት፡፡» ይላል፡፡ ይኽ የታሪክ ምስክርነት በድርሳነ ዑራኤል የታኅሣስ ወር ገጽ ፶፩ ቁጥር ፵፬
ላይም ተጽፎ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም የአጤ ዋሻ
ቅድስት ማርያም ካህናት በቃል እንደሚተርኩት በ፰፻፵፪ ዓ.ም. ዮዲት ጉዲት አኵስም ጽዮንን ለማቃጠል ሠራዊቷን አስከትላ ስትዘምት ካህናተ
አኵስም ታቦተ ጽዮንን ይዘው ሲሸሹ ታቦተ ጽዮን በስደት ወደ ዛሬው የምሥራቅ ሸዋው ዟይ
ደሴት ሔዳ በስሟ ደብረ ጽዮን ተብሎ በተሰየመው ደሴት ላይ ለ፵ ዓመታት ከመቀመጧ አስቀድሞ የዮዲት ሠራዊት ወደ አካባቢው
እስኪመጣ ድረስ በአጤ ዋሻ ማርያም ተቀምጣ ነበር፡፡ ይላሉ፡፡
በተጨማሪም
በተአምረ ማርያም ከአባትሽ ከዳዊት ርስት ከኢየሩሳሌም የመጡ የአኵሱም
ካህናት ርስት የሆነችው ከወግዳ ምድር አጤ ዋሻ ናት፡፡ ተብሎ እንደተገለጸው አኵስማውያን ርስታቸው ወደ ሆነችው አጤ
ዋሻ ቅድስት ማርያም በዚያን የችግር ዘመን ታቦተ ጽዮንን አምጥተው አስቀምጠዋታል፡፡ በዚያን ዘመን የአኵስም ንጉሥም ያረፈው
በዚያ በመኾኑ ያረፈበት ዋሻም የአጤ ዋሻ በማለት እንደተጠራ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን
የዕድሜ ባዕለ ጸጋ ብትሆንም እስከ ዛሬ ድረስ ተገቢውን ትኩረት አላገኘችም ወይንም የታሪክ ተመራማሪዎችንና የጸሐፊዎችን ቀልብ
አልሳበችም፡፡
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ለረጅም ዓመታት በዋሻ ውስጥ ስትኖር ቆይታ በአጼ ይኵኖ አምላክ
ዘመነ መንግሥት ከዋሻው ወጥታ በሣር ክዳን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብታለች፡፡ ለረጅም ዘመናት የቆየችበት ዋሻ መግቢያም ከበላዩ
የነበረው ቋጥኝ ድንጋይ ተደርምሶ ዘግቶታል፡፡ ዛሬ ዋሻውን በርቀት ለማየት ካልሆነ በስተቀር ገብቶ ማየት አይቻልም፡፡
ስለዚህም ታቦተ ማርያም የምታርፍበት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በሣር ክዳን ተሠርቷል፡፡ በሣር
ክዳን ለተሠራችው ቤተ ክርስቲያን በዳግማዊ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ራስ ጎበና ዳጬ በዙሪያዋ ያለውን ቦታ በርስትነት ስለሰጧት
የዱቢሳና መቀኝ ተወላጅ የሆኑት አቤቶ ወልዴ ሕዝቡን አስተባብረው የተሻለሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል፡፡
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ባለውለታ ናት፡፡ በስደትና በችግር ዘመናት የአኵስም ጽዮን ጽሌና ንዋያተ ቅድሳትን በመሸሸግ ለዛሬ እንዲደርሱ አድርጋለች፡፡ | |
በተጨማሪም
በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም የኢጣሊያ ሠራዊት ሀገራችንን በወረረበት ወቅት የአዲስ አበባው የመናገሻ ገነተ ጽኔ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ጽሌ በጠላት እንዳይዘረፍ ቄስ መኩሪያ ወልደ ዮሐንስና አጋፍሪ በየነ ወልደ ዮሐንስ የተባሉ ካህናት የአራዳ
ቅዱስ ጊዮርጊስን ጽሌ ወደ አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም በስውር ወስደው አስቀምጠውት ነበር፡፡ አጤ ምኒልክ ወደ አድዋ ሲዘምቱ
ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስን ይዘው ሄደው እንደ ነበር ይታወቃል፡፡ ስለዚህም ኢጣሊያ በአድዋ ያጣችውን ድል ለመበቀል ዳግመኛ ለወረራ
በመጣችበት ወቅት የአኵስም ሐውልትን በዘረፋ ወደ ሮም እንደወሰደችው፣ በገዳማትና በአድባራት ላይ እሳት እንደለኮሰችው፣
አባቶችን እንደፈጀችው በጦርነቱ ወቅት ኢትዮጵያውያንን ሲራዳቸው የነበረውን የአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጽሌ ቢያገኘው ሊያጠፋው
እንደሚችል ስጋት የገባቸው አባቶች ለታቦቱ መሸሸጊያ የመረጡት አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያምን ነበር፡፡
የኢጣሊያ ወራሪ ጦር ከሀገር ሲወጣና ሀገር ሲረጋጋ በ፲፱፻፴፯ ዓ.ም. የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ካህናት ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስን እስከ አዲስ አበባ
ድረስ በእግር ተጉዘው በወታደር አሳጅበው አምጥተው በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት አስረክበዋል፡፡
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ካህናት በአድዋ ጦርነት ዘምቶ የነበረውን የአራዳ ቅዱስ
ጊዮርጊስ ጽሌ ከጠላት ሰውረው በአደራ በማቆየታቸውና በመጨረሻም በብዙህ ድካምና መንገላታት አዲስ አበባ ድረስ አምጥተው
በማስረከባቸው ከንጉሠ ነገሥቱ ሽልማትና በወርቅ የተለበጠ ታቦተ መድኃኔ ዓለም ተሰጥቷቸው ነበር፡፡
ነገር ግን
ሐምሌ ፳፰ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ.ም. በአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ጆሮን ጭው የሚያደርግ አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ፡፡ በዚኽ ዕለት
ጠዋት ከወትሮ በተለየ ኹኔታ የቤተ ክርስቲያኑ በር ተከፍቶ ተገኘ፡፡ ካህናቱ ወደ ውስጥ ሲዘልቁ በደብረ ዘይት በዓል የሚከብሩት
ታቦተ መድኃኔ ዓለም በመንበሩ ላይ አልነበረም፡፡
በኹኔታው
በመደናገጥ ለወረዳውና ለሀገረ ስብከቱ ቤተ ክህነት እንዲኹም ለፖሊስ የመድኃኔ ዓለም ጽሌ መሰረቅ ያሳውቃሉ፡፡ ከዚያም ሀገረ
ስብከቱና ፖሊስ ጉዳዩን እንሚከታተሉ በመግለጽ የአጥቢያው ካህናት በትዕግሥት እንዲጠብቁ ተስፋ ሰጥተው ይሸኟቸዋል፡፡ ይኹን
እንጂ ታቦተ መድኃኔ ዓለም የደረሰበት ሳይታወቅ ዐሥራ ሰባት ዓመታት አለፉ፡፡
በ፳፻፭
ዓ.ም. ጅቡቲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ምሥራቀ ጸሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ለሚገኙ ካህን አንድ ሰው መጥቶ በቤቱ ታቦት
ስለሚገኝ መጥተው እንዲወስዱ ይናገራል፡፡ ጉዳዩን የሰሙት ካህን ሰውየው ራሱ ታቦቱን እንዲያመጣ ሲጠይቁት ታቦቱን መንካት
እንደማይችል ይነግራቸዋል፡፡ ከዚያም ወደ ሰውየው ቤት ካህን በመላክ ታቦቱ መጥቶ በቤተ መቅደስ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ ይኽ
ወደ ጅቡቲ እንዴትና በማን እንደተወሰደ የማይታወቀው ታቦት በላዩ ላይ የአጤ ዋሻ ማርያም ታቦተ መድኃኔ ዓለም መኾኑንና
በ፲፱፻፴፰ ዓ.ም. እንደተቀረጸ የሚገልጽ ጽሑፍ ተጽፎበታል፡፡
የቤትሳሚስ
ሰዎች በዚኽ ቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማን ይችላል? ከእኛስ ወጥቶ ወደ ማን ይሄዳል? በማለት እንደጠየቁት
የጅቡቲ ምሥራቀ ጸሐይ ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ አባ ዮናስ መልከ ጸዴቅ ኅዳር ፫ ቀን በ፳፻፭ ዓ.ም. ጉዳዩን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት በደብዳቤ ያሳውቃሉ፡፡ የጠቅላይ ቤተ
ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብጹእ አቡነ ማቴዎስም በየካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ለአባ ዮናስና በጅቡቲ ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ይኽ ታቦት የቤተ ክርስቲያን
ሀብት በመኾኑ በአስቸኳይ ወደ መንበረ ፓትረያርክ መጥቶ በቅርስና ቤተ መዘክር እንዲቀመጥ የትእዛዝ ደብዳቤ ይጽፋሉ፡፡ ይኽ
መረጃ የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያምን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ ለሚያስተባብሩ ሰዎች ይደርሳል፡፡
መረጃውን የሰሙት ወንድሞችም ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በመሄድ ጉዳዩን እንዲከታተሉ
ሓላፊነት ከተሰጣቸው ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ ጋር እንዲኹም ከአባ ዮናስ በመነጋገር ታቦተ መድኃኔ ዓለም ወደ ሀገሩና ወደ ቀደመ
መንበሩ የሚመለስበትን ኹኔታዎች በማመቻቸት በወርኃ ግንቦት ፳፻፮ ዓ.ም. በበዓለ ማርያም ታቦቱ ወደ ቦታው ተመልሶ በክብረ
በዓሉ ለሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ መብቃቱ አስደናቂ ተአምር ነው፡፡
ለአጤ ዋሻ ማርያም ታቦተ መድኃኔ ዓለም መመለስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ
ብጹእ አቡነ ማቴዎስ፣ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ የጅቡቲ ምሥራቀ ጸሐይ ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ አባ ዮናስ መልከ ጸዴቅና ሌሎች ወንድሞች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
አባቶቻችን በየገዳማቱና አድባራቱ
ለጊዜያዊ ጥቅም ሳይጨነቁ፣ በደዌ እየማቀቁ፣ በረኃብ
እየደቀቁ በወርቅ የተሠሩና እጅግ የከበሩ ንዋየ ቅድሳትን እየጠበቁ ለእኛ አስረክበውናል፡፡ ትውልዱ ግን የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያና ማስፈጸሚያ የኾኑ ንዋየ ቅድስትን ለባዕዳን ቤተ
መዘክር ማድመቂያና ለግለሰቦች መበልጸጊያ እንዲኾን እየሸጠ ሃይማኖቱንና ታሪኩን እያዳከመ ይገኛል፡፡
ታቦተ
መድኃኔ ዓለም ወደ ሀገሩ የተመለሰው በፈቃደ እግዚአብሔር በልዩ ተአምር እንጂ ዱካውን ለማግኘት በተደረገ ፍለጋና ክትትል
አይደለም፡፡ የአጤ ዋሻ ማርያም ታቦተ መድኃኔ ዓለም ጠፍቶ መገኘት፣ ተሰርቆ መመለስ ብዙ ነገሮችን ያስተምረናል፡፡ በመጀመሪያ
በቤተ ክርስቲያን ያለውን የጥበቃ ክፍተት እንዳለበት እንዲኹም የተሰረቁ ንዋየ ቅድሳት ለመፈለግ የሚደረገው ጥረት ደካማ መኾኑን
ያሳየናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸሙ የዝርፊያ ወይንም የስርቆት ድርጊቶችን ለማስቆም እንዲኹም
ዘራፊዎችን ተከታትሎ ለሕግ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት ቀጣይነት የሌለው መኾኑን ማየት እንችላለን፡፡
ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅና የማስጠበቅ ሓላፊነት የካህናትና የቤተ ክህነት ብቻ ሳይኾን
የምእመናንም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ቤተ ክርስቲያናችንን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ መትጋት ይኖርብናል፡፡
የአባቶቻችን
አምላክ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡