Wednesday, September 6, 2017

ቅዱሳት መካናት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአብነት ትምህርት በተዘጋጀው የትምህርና ጥናት ፖሊሲ ላይ የምክክር ጉባኤ ተካሄደ፡፡
                       






በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ለአብነት ትምህርት ቤት የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ እንዲዘጋጅ በተቋቋመው ኮሚቴ ለአንድ ዓመት ሲጠና በቆየው ረቂቅ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ሰነድ ላይ ነሐሴ ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. ከጠዋቱ ሦስት ጀምሮ በመንበረ ፓትረያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በቅዱስ ሲኖዶስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሙሉ ቀን ምክክር ተደርጓል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዐሥራ ስድስት ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የተለያዩ መምሪያ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በተጨማሪም ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ከመቀሌ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ከቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት፣ የአብነት መምህራን ተወካዮች፣ በግል የተጋባዙ ታዋቂ ምሁራንና ሊቃውንት ተገኝተዋል፡፡
ለአብነት ትምህርት ቤቶች የተዘጋጀው ረቂቅ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ የውይይት መርሐ ግብር የተከፈተው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጸሎተ ቡራኬ ነበር፡፡ በመቀጠልም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ቅዱስ ፓትረያርኩ የመክፈቻ ንግግር እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል፡፡ ከቅዱስነታቸው የመክፈቻ ንግግር በኋላ በአብነት ትምህርት ቤት የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ አዘጋጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ በብፁዕ አቡነ ገሪማ ስለ አብነት ትምህርት አጀማመርና ስለጉባኤው ዓላማ ገለጻ ተደርጓል፡፡ ከብፁዕነታቸው ገለጻ ቀጥሎ ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ታሪካዊ ሂደትና ለሀገር ስለሰጠው ጠቀሜታ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ከሻይ ዕረፍት በኋላ ለአብነት ትምህርት የተዘጋጀው ረቂቅ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ በመምህር ሰሎሞን ወንድሙ አማካኝነት ለተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡ ረቂቅ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው በአብነት ትምህርት ቤቶች የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት፣ የልቀት ማዕከላትን ለማደራጀትና ለመፍጠር፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት በዘመናዊ መንገድ ለማደራጀት፣ የመምህራንን የኑሮ ኹኔታ ለማሻሻል፣ ለደቀ መዛሙርቱም መመሪያ አካባቢን ለመፍጠር የሚያስችሉ አቅጣጫዎች እንደሚያመላክት በስፋት ተገልጧል፡፡ ይኽ ፖሊሲ ከጸደቀ በኋላ የሥርዐተ ትምህርት፣ የመማሪያና ማስተማሪያ መጻሕፍት ዝግጅቶችና የማስፈጸሚያ ሰነዶች እንደሚዘጋጁ ተጠቁሟል፡፡
በውይይቱ ላይ ፕሮፌሰር ጥሩ ሰው ተፈራ፣ ዶ/ር ሥርግው ገላው፣ ዶ/ር ኃይለ ገብርኤል ዳኜ፣ ዶ/ር አማረ አስገዶም፣ ዶ/ር እንጉዳይ አደመ፣ ዶ/ር ጉዳይ እምሬ፣ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም፣ ዶ/ር መርሻ አለኸኝ፣ ዶ/ር ትዝታ ሙሉጌታ፣ አቶ ኃይለ ሥላሴ ወልደ ገሪማ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲኹም ዶ/ር አያሌው ሲሳይ፣ አቶ ብርሃኑ ድንቄና ሌሎች ታዋቂ ምሁራን ተገኝተዋል፡፡ በተጨማሪም ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል፣ መልአከ ታቦር ተሾመ ዘርይሁን፣ መምህር ሐዲስ ትኩነህና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የምክክር መድረኩ ታሳታፊ ነበሩ፡፡

በጉባኤው ተሳታፊዎች ይኽ የምክክር መድረክ በቤተ ክርስቲያናችን የመዠመሪያው መኾኑንና ቢዘገይም ጥናቱ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ትግበራ የሚደርስበት ኹኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡ ፕሮፌሰር ጥሩ ሰው ተፈራ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሕፃናት በራሳቸው ፍጥነት የሚማሩበት፣ የንባብ ክሎት የሚያዳብሩበት፣ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ዝግጅት የሚያደርጉበት ትምህርት ቤት ባለቤት በመኾኗ ፖሊሲው ለንባብ ትምህርት ቤቶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ዶክተር ሥርግው ገላው ደግሞ የአብነት ትምህርቱ ዘመኑን የዋጁ አገልጋዮችን ማፍራት በሚያስችል መልክ መሰጠት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ በርካታ የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ረቂቅ ፖሊሲውን ለማዳበር የሚረዱ በርካታ ጠቃሚ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ በውይይት አመቺ የትምህርት ሥርዐት መዘርጋት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በማያያዝም የአብነት ትምህርትን በቀላሉ  ለትውልድ ለማድረስ በአጭር መንገድ ማስተማር ተገቢ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ቅዱስነታቸው የአብነት  ትምህርት ከዘመናዊ  ጋር ካልተቀናጀ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ስለሚኾን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ለጉባኤው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ቅዱስነታቸው ረቂቅ ፖሊሲውን አዘጋጅተው ያቀረቡትን አካላት፣ ለውይይት የቀረበላቸውን ጥሪ አክብረው የመጡትን የጉባኤውን ተሳታፊዎችና የመድረኩን አዘጋጆች አመስግነው መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል፡፡