Thursday, April 12, 2018

ዜና ሕይወት ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል(፲፱፻፳፫ - ፳፻፲ ዓ.ም.)

ኦ እግዚኦ አዕርፍ ነፍሰ አቡነ ምክረ ሥላሴ

የቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል ሥርዐተ ቀብር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትረያርክ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ  ጳጳሳት(ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦ)፣የጠቅላይ ቤተ ክህነትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተለያዩ መምሪያ ኃላፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ሚያዝያ ፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ተፈጽሟል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል ከአባታቸው ከቄሰ ገበዝ ገብረ አማኑኤል እንዳልካቸውና ከእናታቸው ወ/ሮ ማዘንጊያ ገብረ ሥላሴ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ዛሬ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ልዩ ስሙ ባዩ ፉሪ ፈረስ ማሠሪያ   ላፍቶ በተባለ ቦታ ጥር 7 ቀን 1923 ዓ. ም. ተወለዱ፡፡ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤልም ከወላጆቻቸው ሳይለዩ በፉሪ ጽርሐ ንግሥት ቅድስት ሐና ቤተ ክርስቲያን የደብሩ አስተዳዳሪ ከነበሩት ከመምህር ገብረ ጻድቅና ከመሪጌታ ገብረ ሚካኤል ዘንድ በኋላም ከግራጌታ ወልደ ሐና ዘንድ የንባብና የመጀመሪያ ዜማ ትምህርታቸውን ተምረዋል፡፡ አባታቸው ቄሰ ገበዝ ገብረ አማኑኤል እንዳልካቸው አጐታቸውን መምሬ ዘቊስቋምን ተከትለው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በመንበረ መንግሥት (ግቢ) ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ተመድበው ያገለግሉ ነበር፡፡ እርሳቸውም አባታቸውን ተከትለው በመምጣት በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ቤት በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም የአብነት ትምህርት ቤት ገብተው ጾመ ድጓ፣ ድጓና ምእራፍ  ተምረዋል፡፡

በ፲፱፵፩ ዓ.ም. ወደ ደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም ሄደው ከታወቁት የቅኔ መምህር ከአለቃ (በኋላ መልአከ አርያም) ይትባረክ መርሻ ዘንድ ቅኔ ከነአገባቡ ተምረዋል፡፡  በተማሩትም የጸዋትወ ዜማና የቅኔ ሙያ በመንበረ መንግሥት (ግቢ) ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመዘምርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል ከቅኔ ትምህርት ቤት ከተመለሱ በኋላ በ፲፱፵፫ዓ.ም. ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በ፲፱፻፶ ዓ. ም. አጠናቀዋል፡፡ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በሚማሩበት ወቅት በትምህርታቸው አንደኛ ይወጡ ስለነበር ከንጉሠ ነገሥቱ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ሦስት ጊዜ የወርቅ ብዕሮችና የተለያዩ መጻሕፍት ተሸልመዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱም ለከፍተኛ የዘመናዊና የመንፈሳዊ ትምህርት ወደ ግሪክ አገር ተልከው በአቴንስ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ከመደበኛው የነገረ መለኮት ትምህርት በተጨማሪ የግሪክኛና የዕብራይስጥ ቋንቋዎችን  አጥንተዋል፡፡ በ፲፱፻፶፭ዓ.ም. ከአቴንስ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ማዕረግ በማጠናቀቅ የቢዲ(Bachelor of Divinity) ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በመቀጠልም በአሜሪካ አገር ከሚገኘው ዝነኛው ዬል (Yale) ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ የትምህርት ዕድል (Scholarship) አግኝተው ከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ አሜሪካ ሄደዋል፡፡ በዬል (Yale) ዩኒቨርሲቲም  የአንድ ዓመት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የማስትሬት ዲግሪአቸውን አግኝተዋል፡፡

 ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለስምንት ዓመታት በመምህርነትና በአካዳሚ አስተዳደር አገልግለዋል፡፡ በ፲፱፻፷፭ ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለሦስተኛ ዲግሪ (ለዶክትሬት ትምህርት) ወደ እንግሊዝ አገር ተልከዋል፡፡ በ፲፱፻፷፱ዓ.ም. ከአበርዲን (Aberdeen) ዩኒቨርስቲ በታሪክ ትምህርት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (በዛሬው አዲስ አበባ) ዩኒቨርሲቲ ሥር ይተዳደር በነበረው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ የሐዲስ ኪዳንና የግሪክኛ ቋንቋ መምህር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ባደረጉት ጥናትና ምርምር  መሠረት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕርግ ተሰጥቷቸዋል፤ የኮሌጁም ምክትል ዲን ሆነው ተሾመዋል፡፡ 

 ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በሚያስተምሩበት ወቅት ከጀግናው ደጃዝማች ድረስ ሽፈራው ልጅ ከወ/ሮ ዕፀ ገነት ድረስ ጋር በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ጸሎተ ቡራኬ በሥርዐተ ተክሊልና ቅዱስ ቊርባን ጋብቻ ፈጽመዋል፡፡ ጋብቻቸውንም እንደፈጸሙ ያስተምሯቸው ለነበሩት የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች አርአያ ለመኾን ከብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ እጅ የቅስና ሥልጣነ ክህነት ተቀበለዋል፡፡ 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስቲያንን ለማሻሻል በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት መሠረት ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤልን የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አድርገው ሾሟቸው ነበር፡፡ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል ለዶክትሬት ትምህርት ወደ ውጭ አገር እስከ ሄዱ ድረስ በመንበረ ፓትረያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም በአስተዳዳሪነት ሲያገለግሉና ሲያስገለግሉ ቆይተዋል፡፡ የዶክትሬት ዲግሪአቸውን አግኝተው ወደ ውድ አገራቸው ሲመለሱ በኢትዮጵያ በተከሰተው የፖለቲካ ለውጥ የተነሣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲዘጋ ተወሰኖ ስለነበር እርሳቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬስ (የሥነ ጽሑፍ ክፍል) ተባባሪ የመጽሐፍ አርታኢ (ኃላፊ) (Associate Editor) ሆነው ተመደበው ይሠሩ ነበር፡፡ በ፲፱፻፸ ዓ. ም. በባህልና በወጣቶች ሚኒስቴር የባህልና የቅርስ መምሪያ ኃላፊ ኾነው ሠርተዋል፡፡

ከዚያም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንዲሠሩ በመንግሥት ተሹመዋል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነትም አንድ ዓመት ከሦስት ወር ከሠሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው የዩኒቨርሲቲው ፕሬስ መምሪያ ተባባሪ የመጽሐፍ አርታኢ (ኃላፊ) (Associate Editor) ኾነው ሠርተዋል፡፡ ይኽ የተመደቡበት ሥራ ከትምህርታቸውና ከእምነታቸው ጋር ተቃራኒ ሆኖ ስላገኙት በሥራው አልተደሰቱም ነበር፡፡ ስለዚኽም ለእምነታቸውና ለሙያቸው ተስማሚ ሥራ እንዲሰጣቸው ለፈጣሪያቸው በጸሎት ያመለክቱ ነበር፡፡  

ልዑል እግዚአብሔርም ጸሎታቸውን ሰምቷቸው ለችግራቸው በአንድ ሳምንት ውስጥ ምላሽ አገኙ፡፡ የነገረ መለኮት ሊቅ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸውን የግሪክኛንና የዕብራይስጥን ቋንቋዎች አጣርተው የሚያውቁ ምሁር በመሆናቸው በዓለም አቀፉ የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ለምሥራቅ አፍሪካ የትርጉም ሥራ ባለሙያ(Expert)አማካሪ ኾነው እንዲሠሩ ጥያቄ ቀረበላቸው፡፡ እርሳቸውም ጥያቄውን በደስታ ተቀብለው ሥራውን ለመጀመር ወደ ኬንያ ናይሮቢ ሄደዋል፡፡ በዓለም አቀፉ የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ለምሥራቅ አፍሪካ የትርጉም ሥራ አማካሪ ኾነው ጡረታ እስከ ወጡበት እስከ ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ድረስ ለ፳፭ ዓመታት አገልግለዋል፡፡
       
ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል በነበራቸው ዕውቀት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባል በመሆን በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፈጽመዋል፡፡ ለአብነት ያህልም ፡

፩) ከ1960-1968 ዓ.ም. በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር የዓለም ሐዋርያዊና የወንጌል ተልዕኮ  ኮሚሽን (Commission on World Mission and Evangelism) በአባልነት
        
፪) ከ1961-1966 ዓ.ም. በመላ አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር በኢትዮጵያ የከተማና የኢንዱስትሪ ሐዋርያዊ አገልግሎት ኮሚሽን(Urban and Industrial Mission of AACC) በአባልነትና በሊቀ መንበርነት፣
፫) ከ 1970-1974 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በቦርድ አባልነትና በም/ሊቀ መንበርነት
         
፬) ከ1993 ጀምሮ የዓለም የቅዱሳት መጻሕፍት ሥነ ጽሑፍ ማኅበር በአባልነት አገልግለዋል፡፡
፭) ከዓለም አቀፍ ኅብረት ለፍትሕ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ጉዳይ ጋር በመተባበር በኢጣልያን ወረራ ወቅት የሮም ቤተ ክርስቲያን ላደረገችው ድጋፍ የኢትዮጵያን ሕዝብ በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቅና ተገቢውን ካሣ እንድትሰጥ በተጀመረው እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥ አስተባባሪነት በመሥራት ላይ ነበሩ፡፡ 
፮) በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት እየተገኙም ወጣቶችን ያስተምሩ ነበር፡፡
፯) በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ክፍል በተዘጋጁ ዐውደ ጥናቶች ተገኝተው የተለያዩ ጥናቶችን በማቅረብ ወጣቶችን ያስተምሩ ነበር፡፡

ቀሲስ  ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ይማሩባቸውና ያስተምሩባቸው በነበሩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተለያዩ መጻሕፍትን በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አዘጋጅተዋል፡፡ ለአብነት ያህልም ፡-
፩) በ 1964 ዓ.ም. ‹‹ቄርሎስና ሜቶድዮስ በስላቭ ሀገሮች የፈጸሙት ሐዋርያዊ አገልግሎት››"Cyril and Methodius and the Slavonic Mission", (ያልታተመ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ)፡፡
፪) "Western Christian Missions in Ethiopia since the 16th century".  ‹‹የምዕራብ አገሮች ሚስዮናውያን በኢትዮጵያ ከ16ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ››(ያልታተመ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ)፡፡
፫) በ1969 ዓ. ም. ‹‹ቤተ ክርስቲያንና ሚስዮናውያን በኢትዮጵያና በኢጣልያን ጦርነት ጊዜና በኢጣልያ ወረራ ጊዜ እንዲሁም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት›› ያልታተመ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለዶክትሬት የቀረበ መጽሐፍ፡፡ Church and Missions in Ethiopia in Relation to the Ethio-Italian War and the Italian Occupation of Ethiopia and the Second World War (PhD thesis, 1976), now published as Church and Missions in Ethiopia During the Italian Occupation.
፬) በ 2000 ዓ. ም. በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በግእዝ ቋንቋ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ፣ (የታተመ መጽሐፍ)
፭) በ 2000 ዓ. ም.፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ (ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ)፣ አንደኛ መጽሐፍ፣ (የታተመ መጽሐፍ)
፮) በ 2002 ዓ. ም. የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ (ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ)፣ ኹለተኛ መጽሐፍ፡፡ እንደገና በ2005 ዓ. ም. (የታተመ መጽሐፍ)፡፡  
፯) በ 2003 ዓ.ም. የስብከተ ወንጌል ምእላድ (መድበል/ስብስብ)፣(በ2009 ዓ.ም. እንደገና ተሻሽሎ የታተመ መጽሐፍ)፡፡
፰) Church and Missions in Ethiopia during the Italian Occupation 1934-1939 የተባሉትን ሥራዎቻቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል መንፈሳዊ ትምህርት የተማሩበት በደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ እድሳት እንዲደረጉለት እንዲኹም የአረጋውያን መጦሪያ እንዲሠራ በኮሚቴ አባልነት መመሪያ በመስጠት እንዲሁም ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም  ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣትና ቤተሰቦቻቸውን በማስተባበር በሰሜን ሸዋ በቡልጋ አውራጃ በጠራ ወረዳ የሚገኘው የእረገት ማርያምን ቤተ ክርስቲያን ሙሉ እድሳት እንዲደረግለት አድርገዋል፡፡

ቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል በሚኖሩበት በአያት መንደር የአያት ደብረ በረከት ቅድስት ማርያም(ገመናዬ ማርያም) ቤተ ክርስቲያን ከተተከለች ጀምሮ በዘመናዊ አቅድ እንድትታነጽ በነበራቸው ከፍተኛ ጉጉት በርካታ መንፈሳዊ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ የአያት ደብረ በረከት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከነበረችበት ቆርቆሮ መቃኞ ቤት ወጥታ በዘመናዊ አቅድ በታነጸ መቃኞ ቤት እንድትገባ ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የዋናውም ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ግንባታ በፍጥነት እንዲከናወን በነበራቸው ጉጉትም ባለሙያዎችን በማበረታታት፣ ምእመናን በማስተባበር በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ዛሬ በእርሳቸው አሳሳቢነት፣ የገንዘብ ድጋፍና ማበረታቻ የተጀመረው ኹለት ሺህ ምእመናን የሚያስተናግደው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ ሠላሳ በመቶ ተጠናቋል፡፡

ቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል የአያት ደብረ በረከት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀ መንበር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነበራቸው ታላቅ ፍቅርም ዘወትር በሰንበት እንዲሁም በበዓላት ቀን ከደጇ አይለዩም ነበር፡፡ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ተጠናቆ ለማየት ከነበራቸው ጉጉት የተነሣ ግንባታው የደረሰበትን ደረጃ በየጊዜው እየቀረቡ ይከታተሉ ነበር፡፡ በሕመማቸው ወቅትም በቅርብ የሚያውቋቸውን አባቶች አስጠርተው የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ግንባታን አደራ እንዳይቋረጥ፣ በቅርበት ተከታትላችሁ ከፍጻሜ እንዲደርስ አድርጉ፣ አደራ! አደራ! በማለት አስረክበዋል፡፡

ቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል ለብዙዎች መካሪና አስተማሪ፣ ቤተ ክርስቲያንን በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ያገለገሉ መንፈሳዊና የዋሕ አባት ነበሩ፡፡ ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ዕፀገነት ድረስ ጋር  የተረጋጋ ቤተሰብ መሥርተው አንድ ወንድ ልጅ ወልደው አሳድገው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡ በተጨማሪም በርካታ ልጆችን አስተምረው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረሥላሴ በአደረባቸው ሕመም፤ በጸሎትና በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ክርስቶስ ተሰቅሎ ተቀብሮ በትንሣኤው ዓለምን ባዳነበት በዓለ ትንሣኤ ማግስት ማክሰኞ ሚያዝያ ፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. በተወለዱ በ፹፰ ዓመታቸው በዕረፍተ ሥጋ ተለይተውናል፡፡  
የአያት ደብረ በረከት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ፣ የደብሩ ሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ፣ የደብሩ ካህናትና የአጥቢያው ምእመናንና ምእመናት በቀሲስ ዶ/ር ምክረሥላሴ በዕረፍተ ሥጋ መለየት የተሰማቸውን መራር ኀዘን ይገልጻሉ፡፡ ቀሲስ ዶ/ር ምክረሥላሴ መምህራችን፣ አገልጋያችን፣ መካሪያችንና ድጋፋችን ነበሩ፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረሥላሴ በክህነታቸውና በገንዘባቸው የሚያገለግሉን ትሑት፣ አስተዋይና ለጋስ አባታችን ነበሩ፡፡ ዘወትር እሑድ ጠዋት በዐውደ ምሕረት ተቀምጠው ትምህርተ ወንጌል ሲያደምጡ፣ እርሳቸውም ቆመው ሕዝቡን ሲያስተምሩ፣ በክብረ በዓላት በቅኔ ማኅሌት ተገኝተው ሲያገለግሉ ያምናያቸው ጌጣችን፣ ሞገሳችንና ክብራችን ነበሩ፡፡ ዛሬ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ ካህናት፣ ሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ አባላትና ታላቁን አባታችንን በማጣታችን በእጅጉ ተጎድተናል፣ ኀዘናችንም ከባድ ነው፡፡ የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር የአባታችንን ቀሲስ ዶ/ር ምክረሥላሴን ነፍስ በቀኙ ያቁምልን፣ ከቅዱሳን አንድነት ይደምርልን፡፡ በረከታቸውን ያሳድርብን፡፡
ለአባታችንን ለቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል ከፉሪ ጽርሐ ንግሥት ቅድስት ሐና፣ ከደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ቅድስት ማርያም፣ ከመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል፣ ከታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም፣ ከደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ከአያት ደብረ ጸሐይ ቅዱስ ገብርኤል፣ ከአያት ደብረ በረከት ቅድስት ማርያም እንዲኹም ከተለያዩ ገዳማትና አድባራት የመጡ ካህናትና መዘምራን በቤታቸው ተገኝተው ጸሎተ ፍትሐት አድርሰዋል፣ በሥርዐተ ቀብራቸውም ተገኝተዋል፡፡ የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት እንዲኹም የአያት ደብረ በረከት ቅድስት ማርያም ክብረ ቅዱሳን ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን በሥርዐተ ቀብሩ ተገኝተው በዝማሬ ሸኝተዋቸዋል፡፡

የአባታችንን የቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል ሥርዐተ ቀብር ለማስፈጸም ከተለያየ ቦታ የመጣችኹ መንፈሳዊ አባቶች፣ ዘመድ ወዳጅና የአጥቢያችን ምእመናንና ምእመናት እግዚአብሔር ዋጋችኹን ይክፈላችኹ፣ ያክብራችኹ፡፡ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸውም መጽናናትን ይስጥልን፡፡

ኦ እግዚኦ አዕርፍ ነፍሰ አቡነ ምክረ ሥላሴ

          ቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል በተለያዩ አዝማናት

        ቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ጋር

No comments:

Post a Comment