አባ አሥራት መኩሪያ
አባ አሥራት መኩሪያ የሚኖሩት በዛይ ደስያት በሚገኘው በጌቴሴማኒ ደሴት ነው፡፡ አባ አሥራት የተወለዱበትን ቀን፣ ወርና ዓመተ ምሕረት ባያውቁትም ጣልያን ወደ ሀገራችን ከመግባቱ በፊት መወለዳቸውን ቤተሰቦቻቸው እንደነገሯቸው ይናገራሉ፡፡ ዛሬ ዕድሜያቸው ከሰማንያ ዓመት በላይ ነው፡፡ አባ ወደ ዛይ ደስያት የመጡት ዲያቆን በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ በደብረ ጽዮን ደሴት ተምረው መንኵሰው ከብጹዕ አቡነ ሉቃስ ሊቀ ጳጳስ ዘአርሲ ማዕርገ ቅስና ተቀብለዋል፡፡ አባ አሥራት በዛይ ሐይቅ በሚገኘው በደሴተ ጌቴሴማኒ አርባዕቱ እንስሳ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ለአርባ ዓመታት ያህል አገልግለዋል፣ በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
የአባ አሥራት መኵሪያ ሕይወት አጽንኦ በአትን ያስተምራል፡፡ አባ አሥራት በደሴተ ጌቴሴማኒ የሚገኙ ብቸኛ መነኩሴና ካህን ናቸው፡፡ ዛሬ ዕድሜያቸው እየገፋ በመምጣቱ አገልግሎታቸው እየጠፋ ነው፡፡ አባ አሥራት በደሴተ ጌቴሴማኒ አርባዕቱ እንስሳ ቤተ ክርስቲያን ዲያቆናት አፍርተዋል፣ ነገር ግን በሕግ ተወስኖ ወይንም በምንኵስና የሚያገለግል ቄስ ማግኘት ማግኘት አልቻሉም፡፡ የደሴቱ ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ለማስጠመቅና በሞት ለተለዩ ምእመናን ጸሎተ ፍትሐት ለማድረስ በቅርብ የሚያገኙት አባ አሥራትን ብቻ ነው፡፡ አባ አሥራት ለደሴቱ ምእመናን ብቸኛ ቀዳሽ ካህን፣ አጥማቂ፣ የንስሐ አባት፣ አስታራቂ፣ አስተማሪና መካሪ አባት ናቸው፡፡ የጌቴሴማኒ ምእመናን የአባ አሥራትን ዕድሜ መግፋትና መድከም ሲያስቡ የነገ ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ይጨነቃሉ፡፡
ዛሬ አባ አሥራት መኩሪያ በሰንበትና በበዓላት ኪዳን ያደርሳሉ፡፡ ቅዳሴ የሚቀደሰው እንደተገኘ ነው፡፡ ልዑካን ከተሟሉ ይቀደሳል፣ ካልተሟሉ ይታጎላል፡፡ የደሴቱ ነዋሪዎች ያ ካህን አጥተው ቤተ ክርስቲያናቸው ተዘግቶ፣ ልጆቻቸውን ሳያስጠምቁና ሳይቆርቡ በስም ብቻ ክርስቲያን እየተባሉ ይኖሩበት ክፉ ዘመን ተመልሶ እንዳይመጣ ይሰጋሉ፡፡
አባ አሥራት ብቻቸውን በመሆናቸው በጌቴሴማኒ ደሴት የጥምቀት በዓል የሚከበረው ከዛይ ደብረ ጽዮን ደሴት በሚመጡ ካህናት አማካይነት ነው፤ በዓሉ የሚከበረው ወደ ደብረ ጽዮን ደሴት በመሄድ ነው፡፡ በጌቴሴማኒ ደሴት በየዓመቱ ኅዳር 8 ቀን የአርባዕቱ እንስሳ በዓል ይከበራል፡፡ አባ አሥራት በደሴቱ ላይ ብቻቸውን የሚኖሩ በመሆናቸው አመጋገባቸውና አለባበሳቸው እንዲሁም በአጠቃላይ አኗኗራቸው በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የአባ አሥራትን ቀሪ የሕይወት ዘመን የተሻለ ለማድረግ እንዲሁም በዛይ ሐይቅ የሚገኘው ደሴተ ጌቴሴማኒ አርባዕቱ እንስሳ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማጠናከር ደሴቱን በመጎብኘትና ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ መንፈሳዊ ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡
በቸር ይግጠመን፡፡
Amazing story about the devotion and courage of our Father for his faith. I saw the story from the video. We should spread this news to all church followers and help the churches at Zeway Islands. God joob Memihir Solomon....May God give you His Grace and courage to do more....Please remeber me in your prayer....
ReplyDelete