Thursday, August 2, 2012

ዜና ልደቱ ለመምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ

ዜና ልደቱ ለመምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ

 

  መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ በ 08)(8ዓ.ም. በቤጌምድር[1] ክፍለ ሀገር ከመዘምር ተድላ አይቸው ከእናታቸው ከወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ ተወለዱ፡፡ ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው እናትና አባታቸው በሀገሩ በገባው ወረርሽኝ በሽታ ምክንያት በሞት ስለተለዩዋቸው ዕጓለ ማውታ[2] ለመሆን ተገድደዋል፡፡ በአያታቸው ቤት ጥቂት ጊዜ መኖር እንደጀመሩ ወዲያም አያታቸው ዐረፉና ከአባታቸው ታላቅ ወንድም ከአጎታቸው ዘንድ መኖር ጀመሩ፡፡
   ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የክርስትና አባታቸው ዲያቆን ስለነበር ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስዶ ፊደል አዘለቃቸው፡፡  የትምህርት ጣዕም ስለአደረባቸው ቤተ ክርስቲያን ማዘውተር ጀመሩ፡፡
   ቀደም ሲል ወላጆቻቸውን በሞት ተነጥቀው ለጥቂት ጊዜ አያታቸው ቤት ሳሉ ከፍ ያለ ጽኑ ሕመም ታመው ሰውነታቸው አልፎ አልፎ እየተበጣ ፈንድቶ ለጊዜው ሻል ቢላቸውና እግራቸው ተኮራምቶ ሽባ ሆኖ አልዘረጋ ቢል የአያታቸው ቤት አስተዳዳሪ የነበሩ አረጋዊት ባልቴት የከብት ሸሆና[3]? መረቅ አጠጥተው ለተወሰነ ሰዓት ውኃ እንዳይጠጡ ከልክለው በጥም እንዲቆዩ ካደረጉ በኋላ፣ የወሰኑት ሰዓት ሲደርስ ጠላ ጅው አድርገው እንዲጠጡ አድርገው ደክሞአቸው ሲተኙ እግራቸው ተዘርግቶ ሥራቸው ተፈታቶ ሽባ ሆነው ከመቅረት ድነው ተነሡ፡፡
የተማሪ ቤት ሕይወት
   በዚያን ዘመን በወቅቱ የነበሩም ሽማግሌዎች  ይኽ አሁን ታሞ የዳነው በሽታ ዕድሜው ትልቅ ሲሆን እንደገና ያመዋል፡፡ ሲሉ ሲናገሩ የሰሙት ወላጆቻቸው  ከመሞታቸው አስቀድሞ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ስለነበረ ይኽ ልጅ ሕመምተኛ ስለሆነ ቢማር ይሻለዋል፡፡ እያሉ አስተያየት ይሰጡ ነበር፡፡
 ከአያታቸው ሞት በኋላ ለጊዜው ከክርስትና አባታቸው ፊደል ቢዘልቁም ለፍጻሜው ግን ከተወለዱበት ወረዳ ወጥተው ተማሪ ቤት ገቡ፡፡ ፊደል መቁጠር ጀመሩ፡፡ በምግብና በልብስ የሚረዳቸው ስለአጡ ከትውልድ ቀያቸው ርቀው እንደልባቸው ቁራሽና ጥሬ እያቀፈፉ[4]  ትምህርታቸውን በመቀጠል ንባብ ተምረው ዳዊት ደግመው ግብረ ዲቁና ቀጽለው በግምት በ09)02(1912) ዓ.ም. አዲስ አበባ መጥተው በጊዜው ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ከአቡነ ማቴዎስ[5] ግብፃዊ መዓርገ ዲቁና ለመቀበል በቅተዋል፡፡ ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገር ዘልቀው ጣና ባሕር አጠገብ ሰቀለጥ ጊዮርጊስ ከቄስ እንዲኖ ጠለዝማ ማርያም ከመምህር ዘገየ ጾመ ድጓን[6] ተማሩ፡፡
  ቀጥሎ ጉሬዛ ማርያም ከመምህር አድገህ አጫብር ዜማን[7] ተማሩ፡፡ ወደ ዲማ ጊዮርጊስ ዘልቀው በመምህር በላይ ትምህርት ቤት ውስጥ ከመምህር ይሄይስ ቅኔን መማር ጀመሩ፡፡ ወደ ቢቸና ጊዮርጊስም ጎራ ብለው ከመምህር ውብሸት የቅኔውን ትምህርት ሲቀጥሉ ቆዩ፡፡ ከዚያም አልፈው ወደ ዋሸራ[8] ገዳም ዘልቀው ከመምህር ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ገብተው ሲማሩ ከቆዩ በኋላ ወደ ወንጨር ጊዮርጊስ በማዝገም ከመምህር ተስፋ ማርያም የቅኔ ትምህርታቸውን አጠናቀው ጨረሱ፡፡ ከዚያም ወደ ጎንደር ከተማ ተመልሰው ሻሜ ማርያም ከአለቃ ሣህሉ ዘንድ አንድ ዓመት የቁም ጽሕፈትን ተማሩ፡፡ ከዚህ በኋላ በትግራይ ክፍለ ሀገር አክሱም ጽዮን ገዳም ገብተው ከመምህር ገብረ መድኅን በኋላም አቡነ ሰላማ[9] ከተባሉት መዝገበ ቅዳሴ[10] ተማሩ፡፡
   ከአባ ሠርፀ ድንግልና ከመምህር ተክለ ማርያም ሐዲስ[11] ሲማሩ ቆይተው ደብረ ገነት ቀቀማ ገዳም ገብተው ከመምህር ተስፋ ማርያም በሸዋ ክፍለ ሀገር በደብረ ሊባኖስ ገዳምም ከመምህር ተክለ ማርያም ሐዲስን ተምረዋል፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ መጥተው በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ከመምህር ገብረ ማርያም ሐዲስ አጠናቀው ተምረዋል፡፡
   ገና በወጣትነት ዘመናቸው የእግዚአብሔር ፈቃድ ኾኖኑ መንፈስ ቅዱስ አነሣሥቷቸው ዋልድባ ዳልሽሐ ገዳም[12] ገብተው መንፈሳዊ አገልግሎት ፈጽመዋል፡፡ ሐምሌ 7ቀን %90%9 ዓ.ም. በገዳሙ አበምኔት ሕፃኑ ገብረ ሥላሴ በሚባሉት በተስፋ ሐዋርያት መስቀል ቆባቸው ተባርኮ መነኮሱ፡፡ የምንኩስናው አፈጻጸምም ሥርዓቱ በጥንቃቄ ነበርና አመክሮውን[13] አልፈውት ነው ለክብር የበቁት፡፡ ነገር ከሥሩ ውኃ ከጥሩ በማለት በምሳሌ አበው እንደተናገሩት ይኸን ስልት በመከተል ስለ መምህር ገብረ ሥላሴ የምናኔ፣ የምንኵስና ሕይወት ከመነሻው አንሥተን መተረክን እንጀምራለን፡፡
   በጎጃም ክፍለ ሀገር ጣና ደሴት ገሊላ አቡነ ዘካርያስ ገዳም ገብተው ከበአተ ጾም[14] እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ[15] በገዳሙ ውስጥ ከሚኖሩ አበው መነኮሳት ጋር በአንድነት ዳዊት እየደገሙ ሲያገለግሉ ቆይተው መንፈስ ቅዱስ አነሣሥቷቸው ዋልድባ ዳልሽሐ ገዳም ለመግባት ሄዱ፡፡ በገዳሙ ሥርዓት በአበው ሕግ እግራቸውን አጥበው ምርፋቅ አግብተው[16]  ወደ ቤተ ክርስቲያን ሳይሄዱ ከመነኮሳት ሳይደበለቁ በሊቀ አበው እጅ ሠርከ ኅብስት[17] እየተሰጣቸው  7 ቀን በሱባዔ ከቆዩ በኋላ ሊቀ አበው ወስደው ጸሎተ ማኅበር ወደሚጸለይበት አበው ፊት አቀረቡአቸው፡፡
  በገዳሙ ሥርዓት መሠረት አሳራጊው ሊቀ ምርፋቅ[18] ወደ ገዳሙ የመጡበትን ሐሳብ ጠየቁዋቸው ጥያቄውም እንዲህ የሚል ነበር፡፡ ደበሎ[19] የለበሱ ተማሪ ስለበሩ፤ አንተ ሕፃን ተማሪ ነህ፣ ዋልድባ በረሀ ገዳም ለምን መጣህ? እግረ ጎዳናህን ስትሄድ ደክሞህ ዐርፈህ ሰንብተህ ለመሄድ ነው? ወይንስ ቸግሮህ እርዳታ ለመጠየቅ ነው[20]?  ወይንስ ከዓለም መንነህ እኛን መስለህ ለመኖር ነውን? ብለው ከጠየቁዋቸው በኋላ መልስ እንዲሰጡበት ተፈቀደላቸው፡፡ መንኜ ነው የመጣሁት፡፡ ብለው አንድ ቃል መለሱላቸው፡፡
     እነርሱም መልሰው ምነናም ቢሆን ነፋሱ ለሰውነት የሚስማማ፣ ምግብ እንደልብ የሚገኝበት፣ ንዳድ የሌለበት[21]፣ ደዌ በሽታ የማይበዛበት፣ ትምህርት ለመቀጠልም ብዙ መምህራን ያሉበት ብዙ ገዳማት ስለአሉ ለምን ወደዚያ አልሄድክም? ይህ ገዳም የፍጹማን ገዳም ነው፡፡ ከሰኔ ማርያም እስከ ኅዳር % ቀን ቋርፍ[22]ጭልቃ[23] እንጂ ሌላ እህል የማይቀመስበት፣ የገባው የማይከርምበት[24]፣ የከረመው የማይባጅበት፣ በንዳድና በደዌ ብዛት ሞት የበዛበት ገዳም መሆኑን አልሰማህምን? አሁንም ሕፃን ነህና ወደ ሌላ ገዳም ብትሄድ ይሻልሃል፡፡ ምክራችንን ተቀበል ቢሏቸው ዐውቄ ነው የመጣሁት እናንተን ያስቻለ አምላክ ያስችለኝ፣ እዚሁ እኖራለሁ፡፡ ብለው መለሱላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ኀዲገ ልማድ፣ መቲረ ፈቃድ አለብህ፡፡
  ኀዲገ ልማድ ማለት ይኽ ዓመሌ ነው፡፡ ይኽ  ይገባኛል፣ ይኽን እሠራለሁ፣ ይኽን አልሠራም ማለት የለብህም፡፡   መቲረ ፈቃድ ማለት በፈቃደ ማኅበር እንጂ በራስህ ፈቃድ የምትሠራው ሥራ የለህም ሲጠሩህ አቤት፣ ሲልኩህ ወዴት ብለህ ለገዳሙ መታዘዝ ነው እንጂ ምክንያት ማቅረብ የለብህም፡፡ የገዳሙ ወፍጮው መጁ[25] ኃያል ነው፣ የሙቀጫው ልጁ[26] ከባድ ነው፡፡ በሊቀ ረድእ[27]፣ በመጋቤ[28]፣ በአበምኔት[29]፣ በመላው ማኅበር ፈቃድና ትእዛዝ ማደር ነው[30] እንጂ በራስህ ፈቃድ ማደር የለም፡፡ ነፍሴን ለሥላሴ፣ ሥጋዬን ለገዳሙ መነኮሳት[31] ብለህ ማደር ነውና ትችላለህ ወይ? እንግዲህ ወደህ ግባ ቢሏቸው እችላለሁ ብለው ወደው ተቀበሉ ፡፡
  ከዚህ በኋላ የትምህርት ችሎታቸውንና ኑሮዋቸውን ጠይቀዋቸዋል፡፡ እርሳቸውም የምኖረው በተማሪ ቤት ነው፡፡ ብለው ትምህርታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡ ማዕርገ ክህነታቸውንም ጠይቀዋቸው ዲያቆን ነኝ ብለው ቢመልሱላቸው ከማን ተቀበልህ? ብለው ጠየቋቸው፡፡ ከግብፃዊው አቡነ ማቴዎስ መሆኑን አስረዱዋቸው ሃይማኖትህስ ምንድነው? የእኛ ሃይማኖት ወልድ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት፣ ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ያለ አባት መወለዱን፣ ሁለት ልደት ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ ብለን እናምናለን፡፡ አንተስ? ብለው ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም 2 ልደት በተዋሕዶ ከበረ ብዬ ነው የማምነው ልጃችሁ ነኝ ብለው መለሱላቸው፡፡ ተገዘት አሏቸው፣ ተገዘቱ[32]፡፡
    እነሱም ከዚህ ሃይማኖት እንዳትናወጥ ብለው ገዘቷቸው፡፡ ከዚህ በኋላ መላው ማኅበር ተነሥተው ቆመው ከፊታቸው እንዲወድቁ አዘዋቸው በግንባራቸው ተደፍተው ጸሎተ ቡራኬ ሲቀበሉ እኛን ያስቻለ አምላከ አበው ያስችልህ ያሰብከውን  ምነና እስከ ፍጻሜ ያድርስልህ፡፡ ብለው ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም[33] ደግመው አቡነ ዘበሰማያት ሰጥተው ናዘው፣ ባርከው ካበቁ በኋላ የመላውን አበው (አባቶች) ጫማ ስመው ቆሙ፡፡ እነበሩበት ቦታ እንዲቀመጡ ታዘው ተቀመጡ፡፡
   ሰአልናከ[34] የተደገመበት መክፈልትና ጠበል ቀምሰው ሲነሡ በአበው (በአባቶች) ፊት ሊቀ አበው እስከ 3 ሰዓት የግል ጸሎትህን ትፈጽማለህ፣ በ3 ሰዓት መጋቢው ባለተስፋ የሥላሴ ልጅ ብለው ሲያጨበጭቡ አቡነ ዘበሰማያትም እንደሆነ፣ ወንጌለ ዮሐንስ እንኳን ትደግም[35] እንደሆነ ልፈጽመው ሳትል መጽሐፍህን እንደያዝክ ሮጠህ መቅረብና የታዘዝኸውን መፈጸም አለብህ ብለው የገዳሙን ሥርዓት አስጠንቅቀው ነገሩዋቸው፡፡
   ከዚያም በኋላ መላው አበው እፊት እፊታቸው እየሄዱ አስከትለዋቸው ቤተ እግዚአብሔር? ደረሱ፡፡ ይህም ማለት የገዳሙ ምግብ የሚዘጋጅበት ማለት ነው፡፡ ደወል ተደውሎ ሁሉም በፋጋ[36] በፋጋቸው መቁነናቸውን[37] ተቀብለው ወደየበዓታቸው ሲሄዱ እሳቸውም የመቁነን መቀበያ ፋጋ ተሰጥቷቸው መቁነናቸውን ተቀብለው ሊቀ አበው እየመሩዋቸው እንደ አንድ መነኩሴ የተዘጋጀላቸውን አንድ ቤት ከፍተው አስረከቧቸው፡፡
  በበነጋው ወስደው ከአጣኙ[38] ጋር አገናኝተው ካህን ነውና ከእርስዎ ጋር ያገልግል ብለው አስተዋወቋቸው፡፡ ከዚህ በኋላ እስከ ሰኔ @ ቀን ቆይተው ከሰኔ @1 ቀን እስከ ኅዳር 6 ቀን ድረስ ቋርፍ ብቻ እየተባለ ጭልቃ ብቻ እየተጠጣ ወደ ሚከረምበት ዳልሸሐ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ተሻግረው ገቡ፡፡
  ሥምረተ አበው[39] እየተጸለየ ሥርዓተ ገዳም እየተነበበ ሰንብተው ሐምሌ 7 ቀን 09)09 ዓ.ም. በገዳሙ አበ ምኔት ሕፃኑ ገብረ ሥላሴ በሚባሉት በተስፋ ሐዋርያት መስቀል ቆባቸው ተባርኮ መነኮሱ፡፡ ከመነኮሱ በኋላ ደወል ደውለው፣ መብራት አብርተው በማዕረግ ዲቁና እየቀደሱ ቀን በዕቅብና ረቂቅ እያረቀቁ[40]  ማገልገል ጀመሩ፡፡ ማደሪያቸውንም በፈቃዳቸው በገዳሙ ድውያን ቤት አድርገው ውኃ ቀድተው፣ ዕንጨት ሰብረው እያቀረቡ፣ ድርጓቸውን[41] ቋርፍ ተቀብለው እያቀረቡላቸው፣ ለማይችሉትም ቋርፉን አሽተው ጭልቃ አጨልቀው እየሰጡ ልብሳቸውን እያጠቡ አንበሳ መደብ እየማሱ ፍቅረ ልባም እያፈሰሱ [42] በረድእነት በማገልገል በማስተናገድ 5 ዓመት ቆይተው ረድኤት፣ በረከትና ምርቃት ተቀብለዋል፡፡
  09)@4 ዓ.ም. በራሳቸው ፈቃድ ሳይሆን በመላው ማኀበር ፈቃድ ባለተስፋ ተብለው ከአበው ቅዱሳን አቡነ ዘበሰማያት ተቀብለው አዲስ አበባ መጥተው  በኢትዮጵያ ከነበሩት ከግብፃዊው ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የቅስና ማዕረግ በዚሁ ዓመት ኀዳር %7 ቀን ተቀብለው  ወደ ዳልሸሐ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ለመመለስ ጉዞ ጀምረው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሲደርሱ ዓይናቸውን ታመው፣ ከባልንጀሮቻቸው ተነጥለው ሰነበቱ፡፡ ዓይናቸውን ሲሻላቸው አዲስ አበባ የቀሩ ባልንጀሮቻቸው አኀው መነኰሳት ስለነበሩ ከእነርሱ ጋር አብረው ለመሄድ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡
    ከደብረዳሞ ከአቡነ አረጋዊ ገዳም የመጡ መነኮሳትና የአብረንታት ገዳም[43] አበ ምኔት መምህር ገብረ እግዚአብሔር የቁምስና ማዕርገ ክህነት[44] ሊቀበሉ ለመቅረብ መዘጋጀታቸውን ነግረዋቸው ዋልድባ ገዳም የብዙ ሕማምና ደዌ ቦታ ከመሆኑም በላይ ለመምጣትም ሩቅ ሥፍራ መሆኑን ተነጋግረው የቁምስና ማዕርገ ክህነት ለመቀበል እንዲቀርቡ ተመክረው አብረው ቀርበው የገዳሙ አበምኔት በሌሉ ጊዜ በገዳሙ የሚመነኩሱ መነኰሳት ቆብ የሚባርክ አለመኖሩን ተመልክተው የቁምስናን ማዕርገ ክህነት ታኀሣሥ 3 ቀን %9)@4 ዓ.ም ከግብፃዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ተቀበሉ፡፡
ዕለ ገጽ 1 ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ
 ከዚያም ተመልሰው ዋልድባ ዳልሸሐ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ገቡ፡፡ የዕቅብና አገልግሎት ሥራቸውን ሳይተው የገዳሙ አጣኝ፣ ቀዳሽ ቄስና፣ አበምኔቱም በሌሉ ጊዜ ቆብ ባራኪ ቆሞስ ሆነው በተግባር ቤትም የሚረዱ መነኮሳት ሲታመሙና በሞትም ሲለዩ በጎደለ እየተተኩ በማገልገል ቆይተው በረከት፣ ረድኤት ተቀብለው ተመርቀዋል፡፡
  ከዚያም በኋላ አክሱም ገዳም ደርሰው አንድ ዓመት በመነኮሳት አንድነት ገብተው በሰዓታትና[45] በቅዳሴ አገልግለዋል፡፡ ደብረ ገነት ቀቀማ ገዳም ገብተውም አገልግለዋል፡፡         
    በደብረ ሊባኖስ ገዳምም በርከት ላለ ዘመን አገልግለዋል፡፡ ዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ተብለው ተሹመው ደብረ ሊባኖስ  ወርደው ሲቀድሱ ከቀዳስያኑ አንዱ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ነበሩ፡፡
  የኢጣልያ ፋሽስት ጦር በወራሪነት ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ አዲስ አበባ ገብተው በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቅዳሴ እየቀደሱ፣ ሰዓታት እየቆሙ እያስታኮቱ[46] በርከት ላለ ጊዜ አገልግለዋል፡፡
   ጠላት ሀገራችንን ለቆ ነጻነት ከተመለሰ በኋላ በቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ ሳይዳ ሆስፒታል[47]  የምስካየ ኀዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦት ከእንግሊዝ አገር ከስደት ተመልሶ በዚሁ ሥፍራ ሲገለገል በነበረበት ወቅት መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ በሰዓታትና በቅዳሴ አገልግለዋል፡፡
   የምስካየ ኀዙናን አለቃ የነበሩት አባ ተክለ ማርያም ስለ ታቦተ መድኃኔ ዓለም ከውጭ የመምጣቱን ታሪክ  የምስካየ ኀዙናን መድኃኒዓለምን ገዳም አመሠራረት የሚገልጽ ማስታወሻ  በተሰኘው መጽሐፋቸው በገጽ #4 ላይ እንዲህ ገልጸውት ነበር
 ያችም በስደት አገር የነበረች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጸሎትና ሥነ ሥርዓት እንዲሁም በዘመነ ስደት ጊዜ ምዕራገ ጸሎት ወመሥዋዕት  የነበረው የዴር ሡልጣን መድኃኔ ዓለም ጽላት ነሐሴ @3 ቀን 09)#3 ዓ.ም. ግርማዊት እቴጌ መነን አዲስ አበባ በገቡበት ቀን አባ ኃይሌ ቡሩክ የተባሉት መነኩሴ ይዘውት ገብተዋል፡፡ ብለዋል፡፡
ቀጥሎም በገጽ '6'8 በምዕራፍ 5 የሚከተለውን የታሪክ ሐተታ አስፍረዋል፡፡ 
ከዚህም በኋላ በቤተ መንግሥት የተለየ ቦታ ተወስኖለት እኒሁ አባ ኃይሌ ቡሩክ የተባሉት መነኩሴ እያጠኑና እየጠበቁ ከቆዩ በኋላ ሚያዝያ @7 ቀን %90#5 ዓ.ም. ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ተብሎ ተሰይሞ ለተበደሉትና ላዘኑት ማረጋጊያ ለሕሙማኑ ማጽናኛ እንዲሆን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ተተከለ፡፡
እንደዚሁም በዚያው በስደት አገር ሲጸለይ የነበረው የጸሎት መጽሐፍና ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኑ ሥነ ሥርዓት ሳይጓደል በክቡር አባቴ ሐና እንዲሁም አባ ኃይሌ ቡሩክ በተባሉት መነኩሴ መሪነትና ኃላፊነት ለሥራው አስፈላጊ ሁነው አዲስ በተቀጠሩ አራት መነኰሳትና አራት ዲያቆናት አቀነባባሪነት ሥራውን ቀጠለ፡፡
የእነዚሁም መነኰሳትና ዲያቆናት የስም ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፡፡
1ኛ. አባ ገብረ ኪዳን
2ኛ. አባ ገብረ ጊዮርጊስ
3ኛ. አባ ተክለ ሃይማኖት
4ኛ. አባ ዐሥራት ሲሆኑ፤ ሲሆኑ ዲያቆናቱ ደግሞ
1ኛ. ጥላሁን ብሩ
2ኛ. አየለ ገብሬ
3ኛ. ሥልጣን ወልደገብርኤል
4ኛ. ወልደ ዮሐንስ ይባሉ ነበር ብለዋል፡፡
  በዚህ ታሪክ ውስጥ የመምህር ገብረ ሥላሴ ታሪክ አለመጠቀሱ ስለምን ይሆን?! ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ በጊዜው የነበሩትን  ንጉሠ ነገሥት በመፍራት መኾኑ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም በኋላ ታሪካቸው እንደሚገለጸው እንደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ ፊት አይተው  የማያደሉ፣ ሹመት ሽልማት፣ ጥሪት ቁሪት የማይፈልጉ ቆራጥ ሐዋርያ፣ መምህር ወመገሥጽ ዘኢያድሉ ለገጽ ስለነበሩ ጸሐፊው ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ላለመጋጨት ብለው ስማቸው ከታሪክ መዝገብ እንዲፋቅ አድርገዋል፡፡
    ነገር ግን ታቦተ መድኃኔ ዓለምን ከውጭ ወደ አገር ሲገባ ከተቀበሉት ልኡካን  ከእነ አባ ኃይሌ ቡሩክና ከእነ አባ ገብረ ኪዳን ጋር መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላም አብረው ነበሩ፡፡ ለዚሁም ምስክር እነ አባ ገብረ ኪዳን መሆናቸው የታወቀ ነበር፡፡
    ኹኖም በተራራ ላይ ያለች መንደርና በመቅረዝ ላይ ያለች ፋና (መብራት) መሠወር እንደማይቻላቸው ምንም ቢያዳፍኑት ቢቀብሩት እንደ መስቀለ ክርስቶስ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ሐዋርያ የመምህር ገብረ ሥላሴ ዜና ሕይወት ሊደበቅ አልቻለም፡፡
   መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ በራሳቸው ፈቃድ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ተነሥተው ጌታችን ለሐዋርያት የሰጣቸውን መመሪያ ተገንዝበው የክብር ልብስ ካባቸውን አውልቀው ባና[48] ለብሰው ባልንጀራ፣ ወንድም ሳያስከትሉ፣ ስንቅ ሳያንጠለጥሉ በኪሳቸው ብር ሣንቲም ሳይዙ የክብር ምልክት የሆነ ጌጠኛ ቆባቸውን አውልቀው ትንሽ ተርታ ነጠላ ቆብ አድርገው በላዩ ላይ አሮጌ ጨርቅ ጠምጥመው፣ ጫማቸውን አውልቀው በእግራቸው ጎጃም ጣና አጠገብ ሰቀለጥ ጊዮርጊስንና አባይን ተሸግረው ሮቢት በኣታ እንደገናም ወደ አርማጭኾ[49] በመሄድ አንገረባ ጽዮን በተባሉ አብያተ ክርስቲያን በተባሕትዎ ዳዊት ሲደግሙ ሲጸልዩ ቆይተው ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ መላልሶ ራዓይኬ አባግዕየ፣  ረዓይኬ አባግዕትየ፣ ረዓይኬ መሐሰየ[50] ብሎ ምእመናንን እንዲጠብቅ እንዳዘዘው እርሳቸውንም በራእይ ተገልጦ አዟቸዋል፡፡
    ከዚህ በኋላ በትዕዛዘ አምላክ በፈቃደ እግዚእ የታዘዙትን ለመፈጸም በሐዋርያዊ ተልዕኮ በየቤተ ክርስቲያኑ፣ በየለቅሶውና በየገበያው ሳይቀር እየተዘዋወሩ ድሀ ሀብታም በማለት ለሰው ፊት ሳያደሉ፣ የሚፈራውን ሳይፈሩ ትክክለኛውን የወንጌል ቃል በትጋትና በንቃት በጥብዓትና በተቀደሰ ድፍረት ማስተማር ጀመሩ፡፡
    በዚያን ጊዜ በእግራቸው በመጓዝ ሐዋርያዊ ተግባር (ሥራ) የፈጸሙባቸው ሥፍራዎች በቅደም ተከተል እንደሚከተለው ተገልጸዋል፡፡ በመጀመሪያ ከአርማጭኾ ጎንደር፣ ከጎንደር ደብረ ታቦር፣ ከደብረ ታቦር ጋይንት፣ ከጋይንት መቄት፣ ከመቄት በዋድላ ደላንታ በኩል ወሎ፣ በወሎ ብዙ ከአስተማሩ በኋላ ወደ ሳይንት አመሩ፡፡ ከሳይንት እነርቴ፣ ከእነርቴ ጎንቻ፣ ከጎንቻ እነሴ፣ ከእነሴ ሜጫ ወደ አገው ምድር፣ ከአገው ምድር ወደ ጉሬዛ ሞረት ተጓዙ፡፡
  ከጉሬዛ ሞረት ወደ መተከል፣ ከመተከል ወደ ደረቤ፣ ከደረቤ ወደ ሰክሰንጎ መድኃኔዓለም፣ ከሰክሰንጎ ወደ ጉባይ ሄዱ፡፡ ከጉባይ ወደ ደጀን፣ ከደጀን ወደ ገርበ ጉራቻ፣ ከገርበ ጉራቻ ወደ ሜታ ተጓዙ፡፡ ከሜታ ወደ ጎላ ማርያም፣ ከጎላ ማርያም ወደ ጀልዱ፣ ከጀልዱ ወደ አቤቤ ጊዮርጊስ፣ ከአቤቤ ጊዮርጊስ ወደ መታለያ አቦ፣ ከመታለያ አቦ ወደ አዲስ ዓለም፣ ከዚያም ወደ ወለታ?[51]፣ ብዙ አምልኮ ባዕድ የሚበዛባቸውን አጠንክረው ተመላልሰው በብርቱ ተጋድሎ አስተምረዋል፡፡ ቀጥለውም ኤጀርሳ ለፎን፤ ራሬ አቦን፤ ላይ ጊዮርጊስን፣ ጊንጪን፣ አምቦን፣ ሻቦካን፣ አስተምረዋል፡፡ ወደ ወለጋ ክፍለ ሀገርም በማቅናት ከዚያ ገብተው ጅማ ገነቴን፣ ሆሮን፣ ሻቦን[52]፣ ደምቢዶሎን፣ ለቀምቴን እየተመላለሱ አስተምረዋል፡፡
    ከዚህም አልፈው ተርፈው ለወንጌል ድንበር የላትም በማለት ሱዳን በእንግሊዝ ቅኝ በነበረችበት ወቅት በስደት ኬላውን አቋርጠው ቋንቋ በማጥናት በማስተማራቸው እንግሊዞች በሱዳን ለ6 ወራት አሥረዋቸው ነበር፡፡ ከእሥር ሲፈቱ ግብፅ ደርሰው ገዳማተ ግብፅን ተሳልመው ከአበው በረከት ተቀብለው መምጣታቸውን የስብከተ ወንጌል አጋራቸው የነበሩት ባሕታዊ ገብረ ጊዮርጊስ  ትኩነህ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
 ደርግ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት ገርስሶ አልቦ እግዚአብሔር[53] ብሎ በዐመፅ ክህደትን ባወጀ ጊዜ እኚሁ ባሕታዊ በደብረ ሊባኖስ ዘግተው ይኖሩ ነበርና ምእመናንን ወጥተው በክብረ በዓል ሲያስተምሩ የተናገሩት ቃል ስለ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ የሐዋርያነት ጥብዓት ገላጭ በመሆኑ ከዚሁ ላይ ለመጠቀስ ሁኔታው ግድ ብሏል፡፡
   ባሕታዊ ሲያስተምሩ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ላም እንዳየ አንበሳ ናቸው፡፡ የወሊሶው መምህር አባ ወልደ ትንሣኤ ግዛው[54] ደግሞ ፍየል እንዳየ ነብር ናቸው፡፡› እኔም በዐቅሜ በግ እንዳየ ተኩላ ነኝ፡፡ በማለት በምሳሌያዊ አነጋገር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ወደ ጥንተ ነገሩ እንመለስና መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ ከአምልኮ ባዕድ አምላኪዎችና በእነርሱ ከሚመሩ ጠንቋዮችና ባለዛሮች ጋር በመፋለም በአስተማሩት ተግሣጽና ምክር ብርቱ ተቃውሞ እየደረሰባቸው በታላቅ መሥዕዋትነት አስተምረዋል፡፡
   ከዚያም ወደ ሸዋ ዘልቀው ሰባት ቤት ጉራጌ ገብተው ምሁር ኢየሱስ ገዳም ድረስ እየተዘዋወሩ እየተመላለሱ አስተምረዋል፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ ዓለም  ማርያም ተመልሰው ሆለታን ደግመው ሲያስተምሩ ቆይተው በቀጥታ አዲስ አበባ ገብተው ማስተማር ጀምረዋል፡፡ ለማስተማር የተነሣሡትም ባዕድ አምልኮን ለማጥፋት ከባለ ዛሮችና ጠንቋዮች ጋር ሲፋለሙ እነዚያ ለመንግሥት የሚገብሩትን ሞዓ አንበሳ[55] የሚል የንጉሡ ማኅተም ያለበትን ደረሰኝ በማሳየት እንደ ጋሻ አንግበው ሕጋዊ አቋም እንዳላቸው ስለተከራከሯቸው ፈቃድ ሰጪው አካል ያለው አዲስ አበባ ስለሆነ በግልጥ ለመገሠጽና ሰማዕትነትን ለመቀበል ስለፈለጉ ነበር፡፡
   ለጠንቋዮችና ለዝሙት አዳሪዎች አዲስ አበባ በሀገር ፍቅር አካባቢ በነበረው በመኰንን ሀብተ ወልድ[56] በሚተዳደረው ተቋም የግብሩ ሰነድ ፈቃድ ጭምር መሰጠቱ የአደባባይ ምሥጢር ነበር፡፡
 በመሆኑም በአፉ የክርስቲያን መንግሥት ነኝ የቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ነኝ የሚለው ገዢ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለሚፋለሙ የአጋንንት ፈረሶች ፈቃድ እየሰጠ ግብር እየሰበሰበ የጥፋት መሪና አብነት ስለሆነ ለመገሠጽ በአጭር ታጥቀው ከለሜዳ[57] ለብሰው የሰማዕትነት ተጋድሎአቸውን ቀጠሉ፡፡



[1] ዛሬ ጎንደር በሚባለው አካባቢ
[2] ወላጆቹን  በሞት ያጣ ሕጻን
[3] የበሬ ቅልጥም ለማለት ሳይኾን አይቀርም፡፡
[4] ከየመንደሩ እየለመኑ
[5] አጤ ምኒልክን በእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅደስት ማርያም ቀብተው ያነገሡት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡
[6] ጾመ ድጓ የቅዱስ ያሬድ ሁለተኛው ድርሰት ሲሆን በመጽሐፍ የሚጠናና በዐቢይ ጾም የሚደረስ የምስጋና ጸሎት ነው፡፡
[7] አጫብር፡- በቤተ ክርስቲያን ከሚታወቁት ቤተልሔም፣ ቆሜ፣ ፋኖ፣ ተጉለቴ፣ ወንጨሬ ወዘተ ተብለው በየአካባቢው ከሚታወቁት የዜማ ቤቶች አንዱ ነው፡፡ ይኽ ዜማ በጎጃም አካባቢ በስፋት የሚታወቅ የዜማ ስልት ነው፡፡ በአቋቋም ቤት  ደግሞ ላይ ቤት፣ ታች ቤት፣ ተክሌ፣ ሳንኳ፣ ፋኖ እየተባለ ሲከፋፈል ይታያል፡፡ የጸሎተ ቅዳሴውም ዜማ የሰደድኩላ፣ የአጫብርና የደብረ ዓባይ ተብሎ ይከፈላል፡፡ ሰሎሞን ወንድሙ(09)(8@4)፡፡ የቅዱስ ያሬድ ዜና ሕይወት በተለያዩ ጸሐፍት ሥራዎች፡፡ ሆራይዘን ማተሚያ ቤት፡፡  
[8] በጎጃም የሚገኝ ታዋቂ የቅኔ ጉባኤ ቤት ነው፡፡
[9] ብፁዕ አቡነ ሰላማ ቀዳማይ ጳጳስ ከ08)^5 -09)#5 ዓ.ም. ነበሩ፡፡ በአክሱም መምህር ገብረ መድኀን እየተባሉ በቅዳሴ መምህርነት ያገለግሉ ነበር፡፡ አንዳንድ ምንጮች ስማቸውን መምህር ገብረ አምላክ ይላሉ፡፡
[10] መዝገብ ቅዳሴ- በመጽሐፈ ቅዳሴ የተጻፈውን ገጸ ንባብ በሦስቱ አርእስተ ዜማዎች በነጠላና በድርብ በዜማ የሚያመለክት፣ የዜማ ሥረዮችን በዝርዝር የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ይኽንን የቀጸለ መዝገበ ቅዳሴ ያውቃል ይባላል፡፡ 
[11]  የሒዲስ ኪዳን የትርጓሜ መጻሕፍት ማለት ነው፡፡
[12]ዋልድባ በሰሜን ጎንደርና በምዕራብ ትግራይ አኅጉረ ስብከት የሚገኝ ታላቅና ሰፊ ገዳም ነው፡፡ የገዳሙ ታሪክ የሚጀምረው ከቅድመ ልደተ ክርስቶስ ነው፡፡ በኋላ ዘመን ተነሥተው ገዳሙን ያቀኑትና ዛሬ ዋልድባ በመባል በወል ስም የሚታወቀው ገዳም መሥራች አባ ሳሙኤል ዘዋሊ ናቸው፡፡ በገዳሙ ዋልድባ አብረንታንት ኪዳነ ምሕረት፣ ዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረትና ዋልድባ ዳልሽሐ ኪዳነ ምሕረት የሚባሉ የየራሳቸው አብያተ መቃድስ ያላቸው ማኅበረ መነኰሳት ይገኛሉ፡፡ ማኅበራቱ ቤተ ሚናስና ቤተ ጣዕማ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ዋልድባ ዳልሸሐ ኪዳነ ምሕረት በገዳሙ ከሚገኙት ማኅበር አንዱ ነው፡፡ በዋልድባ የሚኖሩ አበው ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ሳይደግሙ አይውሉም፡፡
[13] አመክሮ ለምንኵስና የሚዘጋጁ ሰዎች ሥርዓተ ምንኵስና ከመፈጸማቸው አስቀድሞ ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ፣ ሥርዓተ ምንኵስናና ገዳማዊ ሕይወትን በመማር ለቀጣዩ ሕይወት ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት፣ በረድእነት በማገልገል የተለያየ የትሩፋት ሥራ በመሥራት ከአባቶች በረከት የሚቀበሉበትና ሥርዓተ ምንኵስና ለመፈጸም ይኹንታ የሚያገኙበት የቆይታ ጊዜ ነው፡፡
[14] ከዐቢይ ጾም መጀመሪያ ማለት ነው፡፡
[15] ከፋሲካ በኋላ ያለው ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ሃምሳኛ ቀን፣ ከጾመ ሐዋርያት(ሰኔ ጾም) መግቢያ ከሰኞ በፊት ያለው እሑድ ቀን ነው፡፡
[16] ምግብ እንዲበሉ አደረጓቸው፡፡
[17] የዕለት ምግብ
[18] የምግብ ቤት ኃላፊና ጸሎተ ማዕድ የሚያደርሱት አባት
[19] ከበግ ቆዳ ጠጉሩ ሳይገፈፍ የሚዘጋጅ የአብነት ተማሪ ባህላዊ ልብስ
[20] በዚያን ዘመን ገዳማት በምግብ ራሳቸውን የቻሉ ነበሩ፡፡ ከራሳቸው አልፈው በአካባቢያቸው ለሚኖሩ ችግረኞችና ተቸግረው ዕርዳታ ሽተው ለሚመጡ ወገኖች ዕርዳታ ይሰጡ ስለነበር ዕርዳታ ፈልገው የመጡ መኾናቸውን ለመጠየቅ ያቀረቡት ጥያቄ ነው፡፡
[21] የወባ በሽታ የሌሌበት ማለት ሲሆን ንዳድ የሚሉት ትኩሳቱን ነው፡፡
[22]  ቋርፍ በዋልድባ ከሚበቅል የተክል ሥር የሚገኝ፣ በምግብነት የሚያገለግል መራራ ጣዕም ያለውና ከተቀቀለ የደረቀ ሙዝና ከጨው ጋር ተቀላቅሎ የሚበላ የዋልድባ አበው የዘወትር ምግብ ነው፡፡
[23] ጭልቃ፡ የተልባ ወይንም የሰሊጥ ወይንም የኑግ ጭማቂ  ሲኾን በማር ወይንም በስኳር ተለውሶ በተለይ ለኅሙማን የሚሰጥ ምግብ  ነው፡፡ ከሣቴ ብርሃን ተሰማ (09)%1):: የዐማርኛ መዝገበ ቃላት፡፡ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፡፡
[24] ለወጣንያን አስቸጋሪ ቦታ ስለሆነ ብዙዎች ለረዥም ጊዜ መቀመጥ የማይችሉ መሆናቸውን ለመግለጽ በመስከረም የገቡ መናንያን እስከ ክረምት አይቆዩም፡፡ እንዲሁም በክረምት የገቡት እስከ መስከረም አይዘልቁም ለማለት ነው፡፡
[25] ያን ጊዜ በገዳሙ እህል የሚፈጨው በሰው ጉልበት በመሆኑ በእጅ የሚያዘውን የእህል ማድቀቂያውን ትልቅነት ለመግለጽ ነው፡፡
[26] ዘነዘናው ማለታቸው ነው፡፡
[27] ሊቀ ረድእ፡ ገዳም በጉልበታቸው የሚያገለግሉ ወንድሞችና አባቶች የሚያስተባብር ኃላፊ ማለት ነው፡፡
[28] መጋቤ፡ የገዳሙን ማኅበር በምግብ አገልግሎት የሚመራና የገዳሙን አበምኔት በረዳትነት የሚያገለግል ከማኅበረ መነኰሳቱ መካከል ተመርጦ የሚሾም አባት ነው፡፡
[29] አበምኔት፡ ከማኅበረ መነኰሳቱ መካከል በምግባሩ፣ በትሩፋቱና በትምህርቱ ተመርጦ የገዳሙን ማኅበርና አገልግሎት ለመምራት  የሚሾም አባት ነው፡፡
[30] እያንዳንዱ መናኝ በገዳሙ የሚኖረው እንቅስቃሴ የተገደበ ነው፡፡ እያንዳንዱን ነገር ለማከናወን የገዳሙን አበው ፈቃድ ማግኘት ግድ የሚል መሆኑን ለማስረዳት ተነገረ ነው፡፡
[31] አንድ  መናኝ በራሱ ላይ ማዘዝ አይችልም፡፡ መውጣት መግባቱ፣ ሌላውንም ተግባረ ሥጋ ተግባረ ነፍስ ማከናወኑ የሚችለው በማኅበር ፈቃድ ነው፡፡  
[32] ይኽ የሃይማኖት አንድነት ሳይኖራቸው ወደ ገዳሙ የሚመጡትን  ለመለየት እንዲኹም ወደ ማኅበሩ የሚቀላቀሉ ሁሉ የሃይማኖት አንድነታቸውን በመሐላ የሚያረጋግጡበት ሥርዓት ነው፡፡
[33] በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ላይ ተጽፎ የሚገኝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጸለየችው ጸሎት ነው፡፡
[34]  ሰአልናከ በገዳማትና በጽዋ  ማኅበር   ማዕድ ለማባረክ የሚደርስ  ጸሎተ ነው፡፡
[35] በአንዳንድ ገዳማት የሚኖሩ አበው ወንጌለ ዮሐንስ ነገረ መለኮትን አምልቶና አስፍቶ ስለሚናገር እንደ መዝሙረ ዳዊት በየዕለቱ ይደግሙታል፡፡ ለአባ ገብረ ሥላሴ የተነገራቸው ሥርዓት ይህንን ትውፊት መሠረት በማድረግ ነው፡፡
[36] ፋጋ  ምግብ መቀበያ ዕቃ ነው፡፡
[37] መቁነን  ለገዳማውያን ተመጥኖ የሚሰጥ የዕለት ምግብ ነው፡፡
[38] በየዕለቱ ቤተ መቅደሱን ከሚያጥኑ ካህን ጋር
[39] ምረት በዋልድባ ገዳም በብቸኝነት የሚፈጸም ሥርዓት ነው፡፡  ይኽም  ከአቡነ ሳሙኤል ልጅነትን ከገዳሙ ማኅበር አንድነትን ለማግኘት የሚፈጸም ሥርዓት ነው፡፡ በሪሁን ከበደ (09)(3(2)፡የዋልድባ ገዳም ታሪክ፡፡ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤትአዲስ አበባ፡፡
[40] ለመገበሪያ የመጣውን ስንዴ እያደቀቁ
[41] በየዕለቱ የሚሰጣቸውን ምግብ
[42]  በአልጋ ላይ ከተኙ አባቶች ዓይነ ምድር እየተቀበሉ መቅበሪያ ጉድጓድ በማዘጋጀት ዓይነ ምድሩን እየቀበሩ፣ ውኃ ሽንት ተቀብለው እያፈሰሱ
[43] የአብረንታት ገዳም የዋልድባ ገዳም አንዱ አካል ነው፡፡
[44]  ቁምስና በአመክሮ ላለፉ አኃውና አኃት ሥርዓተ ምንኵስና ለማድረስ፣ አዲስ የተሠራ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ለመባረክ የሚሰጥ ማዕርገ ክህነት ነው፡፡ ይህንን ማዕረግ የተቀበሉ አበው ቆሞስ(በነጠላ ቁጥር) ቆሞሳት(በብዙ ቁጥር) በመባል ይጠራሉ፡፡
[45] በርእሰ አድባራት አኵስም ጽዮን ጸሎተ ሰዓታት ከዓመት እስከ ዓመት አይታጎልም፡፡ ሰዓታት ዘወትር ከመንፈቀ ሌሊት ጀምሮ እስከ ንጋት የሚደርስ የማኅበር ጸሎት ነው፡፡ ይህን የማኅበር ጸሎት የሚያደርሱ አገልጋዮች ሰዓታት ቋሚዎች በመባል ይጠራሉ፡፡ ጸሎተ ሰዓታት የመዓልትና የሌሊት ተብሎ ይከፈላል፡፡ የጸሎተ ሰዓታት የቃል ለቃል ትርጉም በየሰዓቱ የሚጸለይ ጸሎት ማለት ነው፡፡
[46] የሠርክ ጸሎት እያደረሱ
[47] አሁኑ ደግሞ የካቲት %2 ሆስፒታል
[48] ማቅ ወይንም በርኖስ
[49] በሰሜን ጎንደር የሚገኝ ሥፍራ ነው፡፡
[50] በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሃያ አንድ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጴጥሮስ  በጎቼን ጠብቅ፣ ግልገሎቼን ጠብቅ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ ፡፡ በማለት የሰጠው ትእዛዝ ነው፡፡
[51] በዛሬው ደቡብ ምዕራብ ሸዋ የሚገኝ ሥፍራ ሳይሆን አይቀርም፡፡
[52] ሻምቡ ለማለት የፈለጉ ይመስላል፡፡
[53] እግዚአብሔር የለም፡፡
[54] አባ ወልደ ትንሣኤ ግዛው በዛሬው ደቡብ ምዕራብ ሸዋ በወሊሶ ከተማ የነበሩ ታላቅ ሀብተ ፈውስ የተሰጣቸው አባት ነበሩ፡፡ አባ ወልደ ትንሣኤ ግዛው ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ተብለው ማዕርገ ጵጵስና ተሹመው ነበር፡፡  አባ ወልደ ትንሣኤ ግዛው ተብለው የተጠሩት በዚያን ጊዜ ማዕርገ ጵጵስና ባለመሾማቸው ነው፡፡
[55] የአጼ ኃያለ ሥላሴ መንግሥት ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ሥዩመ እግዚአብሔር ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ (አሸናፊው የይሁዳ አንበሳ በእግዚአብሔር የተሾመ፣ የተመረጠ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) በመባል ይጠራ ነበር፡፡ ይህ ሥያሜ በአጭሩ ሞዓ አንበሳ እየተባለ ይጠራ ስለነበር በዚያ ልማድ የተነገረ ነው፡፡
[56] የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት የአክሊሉ ሀብተ ወልድ ወንድም ናቸው፡፡
[57] ቀይ ልብስ ለብሰው

No comments:

Post a Comment