አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያምን የምናገኛት በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ ከደብረ ብርሃን ከተማ 14 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ከምትገኘው ጎሸ ባዶ ከተማ በአንድ ሰዓት ተኩል የእግር መንገድ ሄደን ነው፡፡ የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በዘመነ ብሉይ እንደኾነ ይነገራል፡፡ በተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት በ09)(2 ዓ.ም. የታተመው ተአምረ ማርያም ገጽ 4)7 ላይ ከዳዊት ርስት ከኢየሩሳሌም የመጡ የአኵስም ካህናት ርስት የሆነችው ከወግዳ ምድር አጤ ዋሻ ናት፡፡ በማለት አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም የካህናተ አኵስም ርስት መኾኗን፣ እመቤታችን በስደት ከተወደደ ልጇ ጋር መጥታ ያረፈችበትና የባረከችው እንደኾነ ያስረዳል፡፡ በ09)(1ዓ.ም. በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት በታተመው ድርሳነ ዑራኤል ገጽ ፶6 ላይም ይኽ ምሥክርነት በተመሳሳይ ሁኔታ ተወስቷል::
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በስፋት አልጻፈም ወይንም አልተነገረም፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ምእመናን ወደ አካባቢው መሄድ ጀምረዋል፡፡ አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ወሳኝ ክሰተቶችን አስተናግዳለች፡፡ ለምሳሌ በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ዮዲት ተነሥታ የአኵሱምን መንግሥት ስትወርና አብያተ ክርስቲያን ስታቃጥል ካህናተ አኵስም ታቦተ ጽዮንን ይዘው ወደ ሸዋ ምድር በመንዝ፣ መርሐቤቴ እንዲሁም ወደ አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም በስደት በመምጣት ተቀምጠዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ፋሽስት ኢጣልያ ሀገራችንን በወረረበት ወቅት የአራዳ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጽሌን በቂም በቀል እንዳያጠፋው በስውር የተቀመጠው በዚሁ አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡
አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ አብርሃም የእጅ መስቀል፣ የታቦተጽዮን ማደሪያ የነበረ ከእንጨት የተሠራ ድንኳን፣ ሌሎች ቅርሶች የሚገኙባት ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ታቦተ ጽዮን በስደት ዘመን የተቀመጠችበት ዋሻ በሥፍራው ከሚጎበኙ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡
በአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም መስከረም ማርያም፣ ኅዳር ጽዮን፣ አስተርእዮና ግንቦት ማርያም በከፍተኛ ድምቀት የሚከበሩ በዓላት ናቸው፡፡ በዓቢይ ጾም ደግሞ የደብረ ዘይት በዓል በተለየ መንፈሳዊ አገልግሎት ይከበራል፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ አጠገብ የሚገኘው ጠበል ደግሞ በፈዋሽነቱ ይታወቃል፡፡
No comments:
Post a Comment