Wednesday, July 18, 2012

የደቡብ ከዋክብት በዛይ ደስያት - በመምህር ሰሎሞን ወንድሙ መታፈሪያ




ወንድሞችና እህቶች! እንደምን ሰንብታችኋል፡፡ ዛሬ በዛይ ደስያት ስለሚገኙት የደቡብ ከዋክብት ጥቂት ላወጋችሁ ፈለግኩ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

የዛይ ሐይቅ ከአዲስ አበባ ወደ ሐዋሳ በሚዘልቀው ዋና መንገድ 10*5 ኪ.ሜ. ርቀት እንደተጓዝን ከዋናው ከመንገድ በስተቀኝ ይገኛል፡፡ የዛይ ሐይቅን በስተሰሜን የቦራ ተራራ፣ የመቂ ወንዝና ከተማ፣ በስተደቡብ ከቦጨሳ መንደር በስተጀርባ የአሊቶ ተራራ፣ የቡልቡላ ወንዝ፣ በስተምሥራቅ የአርሲ ዞን የገጠር መንደር(ቁልምሳ)ና በስተምዕራብ ደግሞ የዝዋይ ከተማ ያዋስኑታል፡፡
ወደ ዛይ ደስያት ለመሄድ ከከተማው ዋና መንገድ በስተግራ በኩል በመገንጠል ጥቂት እንደተጓዝን በስተቀኝ ያለውን ወደ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ካህናት ማሠልጠኛ ገዳም የሚወስደውን መንገድ ትተን ፊት ለፊት ወደሚታየው የዛይ ሐይቅ ዳርቻ እናመራለን፡፡
የተለያዩ ጸሐፍት ዛይ የሚለውን ስያሜ አመጣጥ በተለያየ መንገድ አስቀምጠውታል፡፡ ለምሳሌ በዶክተር ሀብተ ማርያም መጽሐፍ የተቀመጠው ትውፊት  “ካህናተ አኵሱም ወደ ደስያቱ ሲደርሱ አካባቢው በውሃ ተከቦ በማየታቸው በግእዝ ቋንቋ  ዝ-ማይ- ይህ ውሃ በማለት ለቦታው ስያሜ ሰጡት፡፡ በጊዜ ብዛት ዝማይ የሚለው ስያሜ “ዝዋይ” በሚለው ተለወጠ ይላል (ሀብተማርያም 1986-186)፡፡
በሌላ ወገን ዛይ የሚለው ቃል በዘመን ብዛት የተገኘ እንጂ ጥንተ መገኛው ዝዋይ የሚለው አነጋገር ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ ይኽንንም ሲያስረዱ አኵስማውያን ወደ አካባቢው ሲመጡ ሙቀቱ በጣም እንዳስቸገራቸው ለመግለፅ በግእዝ ቋንቋ ዝ ዋዕይ - ይህ ሙቀት በማለታቸው ቦታው ዝ ዋዕይ የሚለውን ስያሜ አግኝቶ ሲኖር በጊዜ ብዛት ሁለት ቃላት መሆኑ ቀርቶና አጥሮ ዝዋይ ለመባል በቃ ይላል፡፡
ሦስተኛው ትውፊት ደግሞ ይኽን ያስተባብላል፡፡ የዝዋይን የስያሜ አመጣጥ ሲያስረዳም በመጀመሪያ ከታቦተ ጽዮን ጋር ወደ ደስያቱ የመጡት ሰፋሪዎች ቦታው እንደደረሱ የቦታው አቀማመጥ በጣም ስላስደሰታቸው ስሜታቸውን በግእዝ ቋንቋ  ዝ-ዋይ !? በማለት ገለጹ፡፡ ይኸውም ይኽ አስደናቂ'አስገራሚ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ሁለቱ ቃላት ተዋሕደው ዝዋይ የሚለው ስያሜ ተገኘ በማለት ያስረዳል (Zelalem 2001፡22)፡፡
 ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ[1] (1959፡ 202-203) ደግሞ ሁሉንም ደስያት[2] ዛይ ያላቸው ታቦተ ጽዮንን ከአኵስም ይዞ የመጣው አጽቀ ሥላሴ የተባለው አባት እንደሆነ ዘግበዋል (Tuma 1982)፡፡  በተስፋዬ ኤዴቶ መጽሐፍ ደግሞ ዛይ የደስያቱ የጋራ መጠሪያ እንደኾነ ተገልጧል፡፡ ይኽም ሕዝቡ በባህላዊ ጨዋታው እግዜር ቤይዛኔ አተንደረን በዛዬ ሲል በደሴቶች ላይ ያኖረን አምላክ ይመስገን ማለቱ እንደኾነ ያስረዳል፡፡  የደስታ ተክለ ወልድ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ዛይ ማለት ዟ ብሎ የተሰጣ' የተዘረጋ' ከአምስት ደሴት የገጠመ ውሃ በማለት ብያኔውን አስቀምጧል(ደስታ ተክለ ወልድ፡09)^2: 4)*7)[3]:: ስለዚህም በጥንት መጻሕፍት ዝማይ፣ ዝዋዕይ፣ ዟይ ወይንም ዛይ   እየተባለ የሚጠራው ቦታ የዛሬው ዝዋይ መኾኑን ሊታወስ ይገባል፡፡
በዛይ ሐይቅ  ላይ አምስት ደስያት ይገኛሉ፡፡ እነርሱም፡-
 1/ ደብረ ሲና
 2/ ገሊላ
 3/ ደብረ ጽዮን
 4/   አይሱት  
 5/   ጌቴሴማኒ ናቸው፡፡
የግራኝ መሐመድ ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ በአጼ ልብነ ድንግል ዘመን በ1520ዎቹ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ፖርቱጋላዊው ጎብኚ አልቫሬዝ የተለያዩ ገዳማትን፣ አድባራትንና አብያተ ክርስቲያን በመገብኘት ስለ ቄሱ ዮሐንስ The prester John of Indies  በሚል ርዕስ ባዘጋጀው መጽሐፉ ውስጥ በዛይ ደስያት አምስት ገዳማት መኖራቸውን ጽፏል፡፡ አልቫሬዝ በዛይ ሐይቅ ላይ አምስት ደስያት መኖራቸውን ጽፏል፡፡ በተጨማሪም አጼ ልብነ ድንግል[1] ከግራኝ ጋር ለመዋጋት ሲዘጋጁ ድል እንዲቀናቸው በደሴቱ ለሚገኝ ለአንድ ገዳም ስዕለት ተስለው እንደነበርም ጽፏል፡፡
አልቫሬዝ ስለ ቄሱ ዮሐንስ ግዛት ሲናገር ‹‹ባሕር የሚመስል ትልቅ ሐይቅ አለ፣ ከዳር እስከዳር አሻግሮ ማየት አይቻልም፡፡ በውስጡም ደሴት አለው፡፡ በቀድሞ ዘመን በቄሱ ዮሐንስ የታነጸ ገዳምም አለበት፡፡ በገዳሙ መነኮሳት አሉበት፡፡›› በማለት ስለ ዛይ ደሴት ተጨማሪ መረጃ አስፍሯል (Alvares 1961; 435-436)፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ በቄሱ ዮሐንስ የታነጸው ቤተ ክርስቲያን የትኛው እንደሆነ በትክክል ለማወቅ አልተቻለም፡፡
ይሁን እንጂ ከግራኝ ዘመቻ በፊት የተጻፈው የአልቫሬዝም ይኹን በወረራው ወቅት የተጻፈው የአረብ ፋቂህ መረጃዎች በደስያቱ ላይ ገዳማት መኖራቸውን ከመጠቆም ሌላ የገዳማቱን ዝርዝርና የነበሩበትን ኹኔታ አያሳዩም፡፡ በእያንዳንዱ ደሴት ላይ ከአንድ በላይ ቤተ ክርስቲያን ከነበረ እንዲሁም በቄሱ ዮሐንስ  የታነጸ ቤተ ክርስቲያን ከነበረ ታዲያ ዛሬ የት ደረሰ!? ለመኾኑ ከግራኝ ወረራ በኋላ በደስያቱ ላይ አብያተ ክርስቲያንን የሚያጠፋ አንዳች ተፈጥሯዊ ወይንም ሰው ሠራሽ ክስተት ተከስቶ ይኾንን!? ሁለቱም ጸሐፍት ስለዛይ ደስያት የጻፉት በወቅቱ መረጃ ጠይቀው ካገገኙት እንጂ ወደ ደስያቱ ገብተው ካዩትና ከተደረዱት አልነበረም፡፡ ስለዚህም በደስያቱ ላይ ስለነበሩት ገዳማት ያስተላለፉልን መረጃ የተዛባ ወይንም የተጋነነ መሆኑን እንዳንጠራጠር የሚከለክለን ነገር የለም፡፡ ለማንኛውም ይኽንን ማጣራት የሁላችንም በተለይም የታሪክ ተመራማሪዎች ታላቅ የቤት ሥራ ይኾናል፡፡


[1] ከ1500- 1532 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የነገሡ ነበሩ፡፡




[1] ታሪከ ነገሥት ዘዳግማዊ ምኒልክ፡፡  ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ አዲስ  አበባ፡፡
[2] ደስያት- የደሴት ብዙ ቁጥር ነው፡፡
[3] ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፡፡ በሀገረሰብ ቋንቋ፡፡ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፡፡

2 comments:

  1. በቅድሚያ ይህን መንፈሳዊ ብሎግ በመጀመርህ አድናቆቴን እገልጻለሁ። ብሎጉ አስተማሪና አወያይ እንዲሁም አሳታፊ እንዲሆን ምኞቴ ነው። በመቀጠልም በዚህ ንባብ (article) ውስጥ ስለተጠቀሰው ቄሱ ዮሐንስ ጥያቄ ለማቅረብ እወዳለሁ። ቀሱ ዮሓንስ ማነው? በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በዚህ ስም የተጠራ ንጉሥ ነበረ ወይ? Indies ማለት የኢትዮጵያ ስም ነውን?...ምናልባትም ይህ ጉዳይ ራሱን የቻለ ንባብ ሊዘጋጅለት የሚችል ቢሆንም ለአሁን ግን ከአንተ ወይም ከብሎግህ አንባቢዎች ምላሽ እንደማገኝ በማመን ነው የምጠይቀው።

    ፍጹም ቸር፣ ፍጹም ፍቅር ኤልሻዳይ አይለየን፤ አሜን።

    ReplyDelete
  2. ውድ ወንድሜ ስለአስተያየትህ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ቄሱ ዮሐንስ በመባል የሚታወቀው ንጉሥ ገብረ ማርያም(ሐርቤ) እንደሆነ የታሪክ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጸሐፊዎች እርሱ አለመሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ታሪኩ ሰፊ በመሆኑ ወደፊት ራሱን ችሎ ለማየት እንሞክራለን፡፡

    ReplyDelete