አባ ገብረ ሥላሴ ተድላን መጀመሪያ ያየኋቸው በ፲፱፻፸1 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በየአሥራ አምስት ቀን እሑድ ይካኼድ በነበረው የአጠቃላይ ጉባኤ መርሐ ግብር ላይ ነበር፡፡ በወቅቱ በጣም ሕጻን በመኾኔ አባ ገብረ ሥላሴ ምን እንዳስተማሩ ትዝ አይለኝም፡፡ ነገር ግን ከጉባኤው በኋላ በዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ሲያስተምሩን ከነበሩ ወንድሞችና እኅቶች ጋር በር ላይ ሲወጡ አግኝተናቸው በርቱ፣ በሃይማኖት ጽኑ! በማለት ጥቂት ምዕዳን ሰጥተውን ባርከውን ተለያየን፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ምክንያት በተሽከርካሪ ጋሪ(wheel chair) ላይ ተቀምጠው ሲያስተምሩ በድጋሚ አይቻቸው ነበር፡፡
በቅብጥ ርትዕት ቤተክርስቲያን በየሩብ ዓመት በሚታተመው የጥናትና ምርምር መጽሔት ኢትዮጵያዊው አባ ገብረ ክርስቶስ በነገረ አረቢ አቡነ አብዱል መሲህ አል ሐበሻ[1] በሚል ርዕስ የተጻፈውን ሳነብ እግዚአብሔር የሚያውቃቸው እኛ የማናውቃቸው በርካታ ቅዱሳን በየገዳማቱ፣ በየዱሩ፣ በየፉርክታውና በከተሞች መኖራቸው ሳይታወቅ ታላላቅ ተጋድሎ ሲፈጽሙ እንደኖሩና እንደሚኖሩ አሰብኩ፡፡ የኢትዮጵያዊው አባ ገብረ ክርስቶስ ታሪክን ለመጻፍ ሠላሳ ዓመታት መፍጀቱን ሳስብ የጸሐፊውን John Watson ጽናትና ትጋት ከልቤ አደንቅኩኝ፡፡
ቅብጣውያን በቤተ ክርስቲያናቸው በመዳከም ላይ የነበረውን ገዳማዊ ሕይወት እንዲያንሠራራ አስተዋጽኦ ያደረጉትን የኢትዮጵያዊውን የአባ ገብረ ክርስቶስን ታሪክ በጽሑፍና በዘጋቢ ምስል ወድምጽ[2] አዘጋጅተው አቅርበዋል፡፡ ቅብጣውያን ዛሬም የአባቶችን ተጋድሎ፣ ትሩፋትና አብነት ያለውን ሕይወት ያጠናሉ፣ ይጽፋሉ፣ ለምእመናንም ያስተዋውቃሉ፡፡ ይኽንን ትውፊታቸውን ሳስብ በጣም እገረማለሁ፣ በመንፈሳዊ ቅንአትም በእኛ ዘንድ ይኽንን ማድረግ የምንጀመረው መቼ ይኾን!? በማለት ራሴን እጠይቃለሁ፡፡
በየገዳማቱና አድባራቱ ለዘመናት ሃይማኖትን ለማጽናት፣ ትምህርተ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ አምልኮተ ጣኦትን ለማጥፋት፣ መልካሙን ገድል የተጋደሉ፣ በጸሎታቸውና በትሩፋታቸው ትውልድ የታደጉ፣ ዳዋ ለብሰው፣ ጤዛ ልስው፣ ድንጋይ ተንተርሰው በመዓልትና በሌሊት ቅድመ ፈጣሪ በእንባና በስግደት ለሀገራቸው፣ ለሕዝባቸው፣ ለቤተ ክርስቲያናቸው ሲጸልዩና ሲማልዱ የኖሩ አበው ዜና ሕይወት በአግባቡ ተዘግቧል ወይንም ተጠንቷል ማለት ያስቸግራል፡፡ ዜና ሕይወታቸው የተጻፈላቸው በጣት የሚቆጠሩ አባቶች ቢኖሩም የተዘጋጁት ሥራዎች ታትመው ለሕዝብ መድረሳቸውን ማረጋገጥ ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም የተዘጋጁት ሥራዎች በውጭ ቋንቋ የተጻፉ በመኾናቸው ወይንም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተጻፉ የመመረቂያ ወረቀት በመኾናቸው አልያም የኅትመት ዕድል ባለማግኘታቸው ለሕዝብ በቀላሉ ሊደርሱ አልቻሉም፡፡
የአንዳንድ አባቶች ዜና ሕይወት በተለያዩ መጽሔቶችና ጋዜጦች ለንባብ ቢበቃም የአባቶችን ታሪክ በማሰባሰብ በአንድነት ተጠርዞ የቀረበ ወጥ ሥራ የለም ማለት ያስደፍራል፡፡ በዲያቆን መርሻ አለኸኝ ዜና ጳጳሳት በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ በዕረፍተ ሥጋ የተለዩ ሊቃነ ጳጳሳት ዜና ሕይወት ብቻ የቀረበ እንጂ በማዕርገ ጵጵስና ያልነበሩትን ነገር ግን ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሀገርና ለወገን ታላላቅ ተግባራት ያከናወኑትን አበው ታሪክ አይዘግብም፡፡ ስለዚህም ይኽንን ክፍተት ለመሙላት ሁላችንም ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡
በ@)4ዓ.ም. የታቦተ ጽዮን የስደት ዘመንና የደቡብ ከዋክብት በዛይ ደስያት የሚለውን መጽሐፍ ለኅትመት ሳዘጋጅ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ በደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ደሴት በግዞት እንደተቀመጡ ያገኘኹትን ፍንጭ መረጃ በማሰባሰብ በስፋት ለመጻፍ አሰብኩ፡፡ ወደ ደሴቱ ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብና የምስል ወድምጽ ቀረጻ ለማካሄድ በሄድኩኝ ጊዜ ከደሴተ ደብረ ጽዮን መምሬ ባንተ ይሁን ሀብተ ማርያም[3] እንዲሁም ከደሴተ ጌተሴማኒ አባ አሥራት መኵሪያ[4] ስለ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ የሚያውቁትን ምሥክርነት በስፋት ሰጡኝ፡፡ ሌሎች አባቶችም ያገኘሁትን መረጃ ትክክለኝነት አረጋገጡልኝ፡፡
ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ደግሞ በአንድ ወቅት በጉባኤ ላይ መምህር ታዬ አብርሃም ስለ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲያስተምሩ አድምጬ ስለነበር ለተጨማሪ መረጃ ጥቅምት @3 ቀን @)4 ዓ.ም. ወደ እርሳቸው ዘንድ ሄጄ ነበር፡፡ የመምህር ታዬ አብርሃም ምሥክርነት ያለምንም ዕረፍት አምስት ሰዓት ተኩል ፈጀ፡፡ ይኽ ምሥክርነት ከሠላሳ ዓመታት በላይ በተሰበሰበ የዓይንና የጆሮ ምስክርነት ላይ የተመሠረተ ከመኾኑም በላይ ባለታሪኩ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ከልደት እስከ አረጋዊነት ዘመናቸው ያሳለፉትን ታሪክ በመምህር ታዬ በተደረገላቸው ቃለ ምልልስ በመቅረጸ ድምጽ ከተቀረጹት ታሪክ የተገኘ ነበር፡፡
በተጨማሪም መምህር ታዬ በቅርብ የሚያውቋቸውን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውን በማነጋገርና ሥዕለ ገጻቸውን በማሰባሰብ የተደራጀና የተጠናከረ ሥራ ሠርተው አገኘሁ፡፡ በመካከል ውይይታችን ለካስ ዛሬም በእኛ መካከል በብዙ ድካምና ጥረት፣ በብርቱ ፍላጎትና ጽናት የአባቶቻችንን ዜና መዋዕል የሚጽፉ አሉ!? በማለት ራሴን ጠየቅኩኝ፡፡
በውይይታችን መጨረሻ ለመምህር ታዬ የዚኽ ሁሉ ድካም መጨረሻው ምንድን ነው!? የዚኽ ሥራስ ዕጣ ፈንታው ምን ሊኾን ነው!? በማለት ወቀሳ አዘል ጥያቄ ሰነዘርኩኝ፡፡ መምህር ታዬም ያደረጉትን ጥረት ገልጸውልኝ አንተም የድርሻህን ተወጣ፡፡ በማለት በወቅቱ ያዩትንና የሰሙትን እንዲህም በግል ማስታወሻቸው የዘገቡትን፣ ከሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለና ከማኅበረ ሥላሴ ጸሐፊ ከአቶ ኃይለ ልዑል ሀብተ ዮሐንስ ያሰበሰቡትን መረጃ ቅጂ አስረከቡኝ፡፡ እኔም መረጃዎቹን ጊዜ ወስጄ በመመልከት ይዘቱን ሳለውጥ መጠነኛ የቅርጽና የቅደም ተከተል ለውጥ በማድረግ ብቻ የመምህር ገብረ ሥላሴ ተድላን ዜና መዋዕል ለንባብ እንዲበቃ አድርጌያለሁ፡፡
የአባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ታሪክ ከኢትዮጵያዊው አባ ገብረ ክርስቶስ ታሪክ ጋር ተመሳሳይ ገጽታ አለው፡፡
ሀ. ታሪካቸው የተጻፈው በሕይወተ ሥጋ ከተለዩ ከሠላሳ ዓመታት በኋላ የተጻፈ መኾኑ፣
ለ. የትውልድና የአገልግሎት ዘመናቸው ተቀራራቢ መኾኑ[5]
ሐ. ሐዋርያዊ ተጋድሏቸውና ገዳማዊ ሕይወታቸው በምእመናን ዘንድ ያለመታወቁ ታሪካቸውን ተመሳሳይ አድርጎታል፡፡
ፖውል ሄንዝ በ1965 ዓ.ም. መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላን በደብረ ጽዮን ደሴት ተግዘው ሳለ በዚያ አግኝቷቸው የዝዋይ ሐይቅና ደስያቱ[6] በተሰኘው ጽሑፉ ላይ ሥዕለ ገጻቸውን አውጥቶት ነበር፡፡
ይኽ መጽሐፍ ደግሞ ከሠላሳ ዓመታት በኋላ የአባ ገብረ ሥላሴ ተድላን ትውልዳቸውና አስተዳደጋቸውን፣ የተማሪ ቤት ሕይወታቸውን ከተማሩበት አካባቢና ከመምህራኑ ሙሉ ስም ጋር ያስተዋውቀናል፡፡ በተለያዩ ገዳማትና አድባራት የነበሩትን የጉባኤ ቤቶችና መምህራንን ይነግረናል፡፡ ይኽም መጽሐፉ ለሌሎች ጥናቶች በመረጃ ምንጭነት እንዲያገለግል ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ በሕይወተ ሥጋ በነበሩበት ዘመን በቃለ መጠይቅ ታሪካቸውን እንዲተርኩ ተደርጎ በመቅረጸ ድምጽ የተቀዳው ምላሻቸው ይኽንን ዜና መዋዕል ለመጻፍ በመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ምንጭነት አግልግሏል፡፡
ዳግመኛም ከተማሪዎቻቸው ከመምህር ታዬ አብርሃም፣ ከሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለና የማኅበረ ሥላሴ ጸሐፊ ከነበሩት ከአቶ ኃይለ ልዑል ሀብተ ዮሐንስ የተገኙ መረጃዎች በመጽሐፍ ዝግጅቱ ተካተዋል፡፡
በመጨረሻም ተማሪዎቻቸው በየዕለቱ በተለያዩ ጉባኤያት በመገኘት በጆሮአቸው የሰሙትን የቃላቸውን ትምህርት፣ በዓይናቸው የተመለከቱትን ድርጊት በግል ማስታወሻቸው ያሠፈሩትን መረጃ እንዲሁም አባ ገብረ ሥላሴ ተድላን በቅርበት የሚያውቋቸውና በወቅቱ በተፈጸሙ የተለያዩ አጋጣሚዎች ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸውን ሰዎች በቃለ መጠይቅ በማሳተፍ የተገኘውን መረጃ በመተንተንና በማጣራት የአባ ገብረ ሥላሴን ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በተለያዩ ጸሐፍት የተጻፉና ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን የኅትመት ውጤቶችም በማብራሪያነት በግርጌ ማስታወሻ ላይ ቀርበዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የአበው ታሪክ በመኾኑ መጽሐፉ በአጼ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የነበረችበትንና ያለፈችበትን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ውጣ ውረድ በወፍ በረር ያስቃኛል፡፡ በዚያን ዘመን ከነበሩት ባሕታውያን እነ አባ ቸርነትን እነ ባሕታዊ ገብረ ጊዮርጊስ ትኩነህን፣ ከሰባክያን እነ አለቃ ኤልያስ ነቢየ ልዑልን በማንሣት አለባበሳቸውን አነጋገራቸውን ሳይቀር ያስተዋውቀናል፡፡ በተጨማሪም አባ ገብረ ሥላሴ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት በእግራቸው የተጓዙበትን ሥፍራ በቅደም ተከተል፣ በአድካሚውና በፈታኝ የገጠርና የከተማ የስብከተ ወንጌል የአገልግሎት ሕይወት ያሳለፉት ፈተናና የነበራቸውን መንፈሳዊ ጥብአት ያሳየናል፡፡
መጽሐፉ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ከቤተ መንግሥት፣ ከመሳፍንቱ፣ ከቤተ ክህነት፣ ከቃልቻዎች፣ ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ያረደጉት ብርቱ ተጋድሎ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት የከፈሉትን መሥዋዕትነት በመዘርዘር ለዘመኑ ሰባክያን አብነት ያሳያል፡፡
በተጨማሪም የሰበካ ጉባኤ ማቋቋም ያለውን ጠቀሜታ በማስረዳትና ሐሳብ በማመንጨት ያደረጉትን አስተዋጽኦ፣ ትኅርምታቸውንና ተጋድሏቸውን፣ አርቆ አስተዋይነታቸውንና ቋንቋቸውን፣ አለባበሳቸውን፣ አመጋገባቸውና ተጋድሏቸውን በዝርዝር በመግለጽ በዓይነ ሕሊናችን እንድንሥላቸው ያስችልናል፡፡ በዘመናችን የነበሩና ያሉ አባቶችን ዜና ለመጻፍም ያነሳሣል፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ከሌሎች ሰዎች በቀጥታ የተወሰደ ንግግር፣ ሐሳብና ምሥክርነት በጉልህና በደማቅ ቀለም እንዲጻፉ ተደርጓል፡፡ ለአንባብያን ተጨማሪ ግንዛቤ የሚሰጡ መረጃዎች በግርጌ ማስታወሻ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ በዋቢነት የቀረቡ ሥራዎችን በተመለከተ በመጀመሪያ ለተጠቀሰ ምንጭ አስቀድሞ የጸሐፊውን ወይንም የአሳታሚውን ሙሉ ስም፣ ቀጥሎ የታተመበትን ዘመን፣ ከዚያም ሐሳቡ የተገኘበትን ገጽ፣ በመጨረሻም የመጽሐፉ ርዕስና የታተመበትን ቦታ የሚያሳዩ መረጃዎች በግርጌ ማስታወሻነት የተቀመጡ ሲሆን፣ ለሁለተኛ ጊዜ ወይንም በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ምንጮች ካሉ የተጻፈው የጸሐፊው ወይንም የአሳታሚው የመጀመሪያ ስም፣ የታተመበት ዘመንና ሓሳቡ የተገኘበት ገጽ ብቻ ነው፡፡
[1]John Watson. Abdel- Mesih al Habashi(Abuna)c. 1898 to c.1973 Orthodox Ethiopia/ Eritrea/ Egypt. In Coptic Church Review: A Ouarterly of Contemporary Patristic studies, Vol.27, No.2 (Summer 2006).
[2] Documentary film
[3] መምሬ ባንተ ይሁን ሀብተ ማርያም በዛይ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ደሴት ተወልደው በዲቁና ዛሬ ደግሞ በቅስና የሚያገለግሉ አባት ሲኾኑ ከአባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ጋር የቅርብ ትውውቅ ነበራቸው፡፡
[4] አባ አሥራት መኵሪያ በዛይ ደስያት ከሃምሳ ዓመት በላይ የኖሩ በዲቁና ወደ ደብረ ጽዮን ደሴት መጥተው በደሴቱ መንኵሰው ሲያገለግሉ የኖሩና ዛሬም በጌቴሴማኒ አርባዕቱ እንስሳ ቤተ ክርስቲያን በማገልገል ላይ የሚገኙ አባት ናቸው፡፡ አባ አሥራት አባ ገብረ ሥላሴ ተድላን በቅርበት ያውቋቸውና ይላላኳቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡
[5] ኢትዮጵያዊው አባ ገብረ ክርስቶስ ከ08)( ዓ.ም. እስከ 09)^5ዓ.ም. ነበሩ፡፡ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ከ08)(8ዓ.ም. እስከ 09)*2ዓ.ም. ነበሩ፡፡
[6] Paul B. Henze (1973). Lake Zway and its Islands: An Ethiopian Lake wUnique Christian Culture has Survived since medieval times. in Ethiopian Observer Vol. XVI
ሊታወሱ የሚገባቸውንና በረከታቸው የሚያስፈልገንን እንዲህ ዓይነት አባቶች ለማስተዋወቅ በመጀመርህ እግዚአብሄር ጸጋውን ያብዛልህ። ከንባቡ ውስጥ የሚከተለውን ዓረፍተ ነገር ሳነብ አስተያየት እንዳቀርብ አነሳሳኝ።
ReplyDelete"ፖውል ሄንዝ በ1965 ዓ.ም. መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላን በደብረ ጽዮን ደሴት ተግዘው ሳለ በዚያ አግኝቷቸው የዝዋይ ሐይቅና ደስያቱ በተሰኘው ጽሑፉ ላይ ሥዕለ ገጻቸውን አውጥቶት ነበር፡፡"
አስተያየቴ ታዲያ ይህን ሥዕለ ገጽ (ፎቶ) እዚህ ንባብህ ላይ ብታወጣው ምንኛ መልካም ነበር የሚል ነው።
ይህንና ሌሎች ምስላቸውን ለማውጣት እየጠበቅኩኝ ነው፡፡ በቅርቡ ይወጣል፡፡
DeleteI will post it very soon.
ReplyDelete