Friday, July 27, 2012

አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም

የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያምን የምናገኛት በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ ከደብረ ብርሃን ከተማ 14 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ከምትገኘው ጎሸ ባዶ ከተማ በአንድ ሰዓት ተኩል የእግር መንገድ  ሄደን  ነው፡፡ የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በዘመነ ብሉይ እንደኾነ ይነገራል፡፡ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት በ09)(2 ዓ.ም. የታተመው ተአምረ  ማርያም ገጽ 4)7 ላይ   ከዳዊት ርስት ከኢየሩሳሌም የመጡ የአኵስም ካህናት ርስት የሆነችው ከወግዳ ምድር አጤ ዋሻ ናት፡፡ በማለት አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም የካህናተ አኵስም ርስት መኾኗን፣ እመቤታችን በስደት ከተወደደ ልጇ ጋር መጥታ ያረፈችበትና የባረከችው እንደኾነ ያስረዳል፡፡ 09)(1ዓ.ም. ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት በታተመው  ድርሳነ  ዑራኤል  ገጽ6 ላይም ይኽ ምሥክርነት በተመሳሳይ ሁኔታ  ተወስቷል::
የአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በስፋት አልጻፈም ወይንም አልተነገረም፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ምእመናን ወደ አካባቢው መሄድ ጀምረዋል፡፡ አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ወሳኝ ክሰተቶችን አስተናግዳለች፡፡ ለምሳሌ  በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ዮዲት ተነሥታ የአኵሱምን መንግሥት ስትወርና አብያተ ክርስቲያን ስታቃጥል ካህናተ አኵስም ታቦተ ጽዮንን ይዘው ወደ ሸዋ ምድር በመንዝ፣ መርሐቤቴ እንዲሁም ወደ አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም በስደት በመምጣት ተቀምጠዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ፋሽስት ኢጣልያ ሀገራችንን በወረረበት ወቅት የአራዳ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጽሌን በቂም በቀል እንዳያጠፋው በስውር የተቀመጠው በዚሁ አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡
 አጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ አብርሃም የእጅ መስቀል፣ የታቦተጽዮን ማደሪያ የነበረ ከእንጨት የተሠራ ድንኳን፣ ሌሎች ቅርሶች የሚገኙባት ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ታቦተ ጽዮን በስደት ዘመን የተቀመጠችበት ዋሻ በሥፍራው ከሚጎበኙ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡
 በአጤ ዋሻ ቅድስት ማርያም መስከረም ማርያም፣ ኅዳር ጽዮን፣ አስተርእዮና ግንቦት ማርያም በከፍተኛ ድምቀት የሚከበሩ በዓላት ናቸው፡፡ በዓቢይ ጾም ደግሞ የደብረ ዘይት በዓል በተለየ መንፈሳዊ አገልግሎት ይከበራል፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ አጠገብ የሚገኘው ጠበል ደግሞ በፈዋሽነቱ ይታወቃል፡፡

Monday, July 23, 2012

ዜና ሕይወቱ ለብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ(፲፱፻፴፪ — ፲፱፻፹፪)

ዜና ሕይወቱ ለብጹዕ  አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ 

           (፲፱፻፴፪፲፱፻፹፪)

            


በጸሎተ ቅዳሴ አስቀድመው ስላረፉ ወገኖች እንለምናለን፡፡  የቅዱሳንን ሕይወት እናስታውሳለን፡፡ ዜና አበውን መጻፍ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትውፊት አለው፡፡ የቅድስት፣ አሐቲ፣ ሐዋርያዊትና እንተ ላዕለ ሉ ቤተ ክርስቲያን አበው በዘመነ ብሉይ በዜና መዋዕል፣ በዘመነ ሐዲስ በግብረ ሐዋርያትና  በዘመነ ሊቃውንት -  በስንክሳርና በገድላት የተጻፉትን አበው የተጋድሎ ሕይወት በማንሣት ምእመናንን ለማስተማር ይጠቀሙበታል፡፡ ይህ ትውፊት በዘመናችንም የተለያዩ አባቶችን ዜና ሕይወት አንሥተን እንድንነጋገር አስችሎናል፡፡
የአባቶችን ታሪክ ምን እናጠናለን?
       ፈጣሪያችንን እንዴትና ለምን እንደምናመልክ ለመማር
       በፈተና ለመጽናትና ለተጋድሎ ለመዘጋጀት
       ከአበው በረከትና ረድኤት ለመሳተፍ
       ሕይወታችንን ለማየት
       ምግባር ትሩፋት ለመማር
       የቤተ ክርስቲያንን ፈተናና ጉዞ ለማየትና ከታሪክ ለመማር ይጠቅመናል፡፡

የወረቀቱ ዐበይት ዓላማዎች
          የብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ አጭር የሕይወት ታሪክን ማስቃኘት
          ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በሕይወተ ሥጋ በነበሩበት ዘመን በቤተ ክርስቲያን የነበረውን አጠቃላይ ሁኔታ በወፍ በረር  ማሳየት ነው፡፡

የወረቀቱ ውሱንነት

          ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ካንቀላፉ ከአሥር ዓመታት በላ በመዘጋጀቱ ብዙ ታሪክ ተዘንግል፡፡
የብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ልደትና አስተዳደግ
          ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በ፲፱፻፴፪ ዓ.ም. ከአቶ ገበየሁ እሰየና ከወ/ሮ አሰለፈች ካሣ በስዕለት በደሴ ከተማ ተወለዱ፡፡ ወላጆቻቸው ልጆች እየወለዱ እየጠፉባቸው ስለተቸገሩ ለሕጻኑ የሰጡት  ስም ተስፋዬ የሚል ነበር፡፡    
          የብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ አጎት የነበሩት አለቃ ድንቁ- አንድ ቀን ሕጻኑ ተስፋዬ ገበየሁ የእንጨት መስቀል ሠርቶ ጓደኞቻቸውን ለማሳለም ሲሞክር፣ በሌላ ቀን ደግሞ  መጽሐፈ ድጓቸውን ገልጠው ሲመለከት በማየታቸው ዕድሜ ሰጥቶኝ የዚህን ሕጻን መጨረሻ ባሳየኝ በማለት ተናግረው እንደነበር ቤተሰቦቻቸው ይገልጻሉ፡፡
          ፊደል የቆጠሩት በደሴ መድኃኔ ዓለም ነበር፡፡
          ከየኔታ ክፍሌ ( አባ ክፍለ ማርያም) ጋር መገናኘታቸው የሕይወት መስመራቸውን ለውጦታል፡፡
          ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በሕጻንነታቸው የኔታ ክፍሌን ተከትለው  ከደሴ መድኃኔ ዓለም ወደ ገነተ ማርያም፣ ከዚያም ወደ ነአቶ ለአብና ወደ አባ ቡሩክ ገዳም ትምህርት ፍለጋ ሄደዋል፡፡
           ከየኔታ ክፍሌ የውዳሴና የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜያትን፣ አዕማደ ምሥጢራትን ባሕረ ሐሳብን ቀጽለዋል፡፡ በተማሪ ቤት ሳሉ ጥያቄና ክርክር ይወዱ እንዲሁም የተነገራቸውን ቀለም ይይዙ ስለነበር በየኔታ ክፍሌ ስማቸው መዝገበ ሥላሴ ክፍሌ ተባለ፡፡
          መዝገበ ሥላሴ ክፍሌ ከብጹእ አቡነ ይስሐቅ ማዕርገ ዲቁና ተቀብለዋል፡፡ በ፲፱፻፶፮ ዓ.ም. ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመምጣት ማዕርገ ምንኵስና ተቀብለዋል፡፡
          በአዲስ ዓለም ደብረ ጽዮን ማርያም ከነበሩት  ከታላቁ የቅኔ መምህር አፈወርቅ መንገሻ ቅኔ ከአገባቡ፣ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከመምህር ፍሥሐና ከመምህር ገብረ ሕይወት የመጻሕፍተ ሐዲሳት ትርጓሜና ትምህርተ ሃይማኖት ከመምህር ቢረሳው ደግሞ መጻሕፍተ ሊቃውንትን አኺደዋል፡፡
          በደብረ ጽጌ ቅድስት ማርያም ከመሪ ጌታ አብተው ላሊታግዳን ምዕራፍ፣ ጾመ ድጓን፣ ከመምህር ልዑል መዝገበ ቅዳሴን ተምረዋል፡፡ በደብረ ሊባኖስ ዳቤ እየጋገሩ አባቶችን አገልግለዋል፡፡ በገዳማዊ ሕይወታቸው የሰገዱበት የእጃቸው ፈለግ ሞፈር የሄደበት የበሬ ጫንቃ ይመስል እንደነበር በገዳም በቅርብ የሚያውቋቸው አበው ይናገራሉ፡፡
          በ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. ከብጹእ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማዕርገ ቅስና ተቀብለዋል፡፡
          ከመምህር ፍሥሐ ወደ ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ተልከው ወደ ሐረርጌ በመሄድ ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ ጎን ለጎን የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
          በ፲፱፻፷፫ ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምህርት በብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ወደ ግሪክ ተልከዋል፡፡
          በደሴተ ፍጥሞ ለሁለት ዓመት መንፈሳዊ ትምህርት ተምረው - ዲፕሎማ ፣ከአቴንስ የኒቨርስቲ - በሥነ መለኮት የማስትሬት ዲግሪ ፣ ከስዊዘርላንድ ፍሪበሪን ዩኒቨርስቲ - በፈረንሳይኛ ቋንቋ የምስክር ወረቀት እንዲሁም በኢየሩሳሌም ደብረ ጽዮን የግሪክ መንፈሳዊ ኮሌጅ- በአረብኛ ቋንቋ የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡
          በኢየሩሳሌም በደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት - የኢትዮጵያውያንን ልጆች በማሰባሰብ ባሕላቸውንና ቋንቋቸውን በማስተማርና የዕጣንና ከርቤ ቅመማ በማካሄድ ለገዳሙ ገቢ ያስገኙ ነበር፡፡
          ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ቤተ ክርስቲያን  በተቸገረችበት ወቅት የተገኙ አባት ነበሩ፡፡
          ብጹዕነታቸው በኢየሩሳሌም አንድ ቀን ሌሊት ከተኙበት ክፍል አንድ ቀላ ያለ ረጅም ሰው ቀስቅሷቸው  አሁን በዚህ የምትቀመጥበት ጊዜ አይደለም፡፡ ወንጌል ለማስተማር  ወደ ኢትዮጵያ እንሂድ ይላቸዋል፡፡ በትእዛዙ ግራ በመጋባት ማንነቱን ሲጠይቁት ኤፍሬም ሶርያዊ ነኝ፡፡ ይላቸዋል፡፡
          ጠዋት ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ  ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥሪ ደረሳቸው፡፡ በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፸፩ ዓ.ም. ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ኤጲስ ቆጶስ ዘሸዋ ተብለው ተሹመዋል፡፡
          ለቅዱስ ሲኖዶስ የመተዳደሪያ ደንብ አዘጋጅተው እንዲጸድቅ በማድረጋቸው የተነሣ ልዩ ልዩ ውንጀላዎች( መንበረ ፓትረያርክ ለመገልበጥ ይፈልጋሉ፣ በርዳታ የተሠጠ ዶላር ወስደዋል፡፡) ቀረበባቸው፡፡ ይህ ሁኔታ ሥራ ሊያሠራቸው ባለመቻሉ ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ለመፋጠን ወደ ዝዋይ ወረዱ፡፡
 የዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ በ1960 ዓ.ም. ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት በተገኘ ርዳታ ግንባታው ተጀምሮ በ1960 ዓ.ም. ተመርቋል፡፡ ከስድስት ዓመታት በኋላ በሀገራችን በተፈጠረው የመንግሥት ለውጥ የተነሣ ተማሪዎቹ ተበትነውና ማሠልጠኛው ተዘግቶ ነበር፡፡ ደርግ ማሠልጠኛውን ለዕድገት በኅብረት ዘመቻ ጣቢያነት አውሎት ነበር፡፡ በ1970 ዓ.ም. ባሕታውያን በከተማ ውስጥ እየተዘዋወሩ በሚያስተምሩት ትምህርት ደርግ ደስተኛ ባለመሆኑ ተሰብስበው ወደ ማሠልጠኛው እንዲገቡ ተድርጎ ነበር፡፡
          በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ከነበሩት አራት የጥበቃ ሠራተኞች አንዱ አቶ ተረፈ አስፋው ነበሩ፡፡
          አቶ ተረፈ አስፋው ማሠልጠኛውን ለሁለት ዓመታት ያለ ደመወዝ ሲጠብቁ በጦር እስከመወጋት ደርሰው ነበር፡፡ ታመውም ከማሰልጠኛው ባለመለየት ለቤተ ክርስቲያን ጠብቀው ያቆዩ ታላቅ ባለውለታ ናቸው፡፡
          ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በሐምሌ 9)1 ዓ.ም. ዝዋይ ሲመጡ በመጀመሪያ ያገኙትና ብዙ የረዷቸው አቶ ተረፈ ነበሩ፡፡
          ለልማት የተሰባሰቡ ባሕታውያን በሊቀ ጳጳሱ ቤት ባሉ መኖሪያ ክፍሎች ተቀምጠው ነበር፡፡ ወደ ዝዋይና አጎራባች ከተሞች በመሄድ የተለያዩ ነገሮችን ይፈጽሙ ነበር፡፡ የልማቱ ሥራ ፈጽሞ አልተሳካም ነበር፡፡ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ የነበሩትን ባሕታውያን መስመር ለማስያዝ ባደረጉት ጥረት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠሟቸዋል፡፡
          ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ወደ ማሠልጠኛው ሲገቡ የተማሪዎች ማደሪያ የሌሊት ወፍ አያስገባም ነበር፡፡ ብጹዕነታቸው ያለምንም በጀት ከገዳማት፣ ከአድባራት፣ ከመንገድ የወደቁትን  እንዲሁም ከአካባቢው ሕጻናትን እያመጡ ማስተማር፣ ማሳደግ ጀመሩ፡፡ መምህራን በመቅጠር የአካባቢውን ሰዎችንም መሠረተ ትምህርት ያስተምሩ ነበር፡፡ በማሠልጠኛው ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ ጸሎት የሚካሄደው በዛፍ ጥላ ሥር ነበር፡፡ ለቅዳሴ የሚሄዱት ከዝዋይ ከተማ ሰባት ኪ.ሜ. ወደ ምትርቀው አዳሚ ቱሉ ደብረ ጸሐይ ቅድስት ማርያም ነበር፡፡
          9)፸፬ ዓ.ም. ቤተ ክርስቲያን፣ የእንግዶች ማረፊያ ቤት፣ ክርስትና ቤት፣ ወፍጮ ቤት በማሠራት በገዳም ሥርዓት እንዲተዳደር አድርገዋል፡፡
          ለትምህርት ወደ ዝዋይ የሚመጣ በበጀት እጥረት አይመለስም ነበር፡፡ በክረምት መኝታ ቤት ሞልቶ በድንኳን እያደሩ የሚማሩ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ብዙዎች ከዝዋይ መለየት አቅቷቸው በዚያው ቀርተዋል፡፡ ዝዋይ ለሸዋ፣ ለአርሲና ለሐረር ካህናት ማሠልጠኛ ማዕከል ሆና ነበር፡፡ ዝዋይ በብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ጥረት ተለውጣ ነበር፡፡
           ንቡረ ዕድ ክፍለ ዮሐንስ መኮንን ቤቴንና ትዳሬን ትቼ ለአራት ዓመት ከስድስት ወር የመነንኩት የብጹዕነታቸውን ትምህርት ፈልጌ ነው፡፡ ዘወትር በፍቅርና በስስት እከተላቸው ነበር፡፡ ገና ለገና ከንፈራቸው ሲንቀሳቀስ ልቤ በሐሴት ይሞላል፡፡ ----    ከዕለት ዕለት እየተደነቅኩ አብሬያቸው እኖር ነበር፡፡ በማለት ይናገራሉ፡፡
          ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የወንጌል አድማስ ዝዋይ አይደለም፡፡ ገና የምናዳርሰው ብዙ ሥፍራ አለ፡፡ በማለት በማሠልጠኛው ክፍለ ጊዜ ተመድቦላቸው በቀኝ እጃቸው በትረ ሙሴ፣ በግራ እጃቸው መስቀልና የሚያስተምሩበትን ጥራዝ ታቅፈው ማንንም ሳያስከትሉ ክፍል ገብተው ያስተምሩ ነበር፡፡ ለትምህርትና ለሥራ ከፍተኛ ትኩረት ስለነበራቸው ብዙ ጊዜ ለሰዎች ቀጠሮ አይሰጡም ነበር፡፡

ዝዋይ በሦስቱ ሕግጋት
ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ሦስት ሕግጋት አውጥተው ነበር፡፡
ሀ. በሥራ  ሰዓት
   ፈረንጆች ገንዘብ የሚሰጡን ራሳችንን እንድንችል ሊያስተምሩን እንጂ ሊጦሩን ፈልገው አይደለም፡፡  በማለት የማሰልጠኛው አገልግሎት ዘላቂነት እንዲኖረው ለደቀ መዛሙርቱ የአትክልት ኩትኳቶና ሌሎች ተግባራትን ያስተምሩ ነበር፡፡  በማሠልጠኛው የተለያየ አትክልት፣ አዝርእትና ፍራፍሬ አልምተዋል፡፡
ለ. በትምህርት ሰዓት
          ለካህናት ማሠልጠኛው ሥርዓተ ትምህርት ቀርጸው፣ የመማሪያና ማስተማሪያ ጥራዝ አዘጋጅተው ያስተምሩ ነበር፡፡
          በ1980 ዓ.ም. 12 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ተቀብለው በክረምት መርሐ ግብር ማስተማር ጀመሩ፡፡

ሐ. በጸሎት ሰዓት
   በዚህ በረሃ የወድቅኩት የማንንም ዶክተር ተስፋ አድርጌ ሳይሆን እመቤቴን ተስፋ አድርጌ ነው፡፡ ወባ መራቢያ ሥፍራ የሙት ልጆች ሰብስቤ የገባሁት ወላዲተ አምላክን ተስፋ አድርጌ ነው፡፡ ጸሎታ ለማርያም ከተባለ በኋላ የሚገባ ሰው ሰይጣን መስሎ ስለሚታየኝ ሰውነቴ ይለዋወጣልና አትፈታተኑኝ፡፡
ደቂቃ ሳይዛነፉ መገኘት ግዴታ ነው፡፡ በሦስቱም ቦታዎች ብጹዕነታቸው ከሰዓቱ ቀድመው ይገኛሉ፡፡  ዘወትር በመኝታ ቤትና በመማሪያ ክፍል በመሄድ ይቆጣጠራሉ፣ ያረፈደ፣ ያልተገኘ ተማሪ ይቀጣል፡፡
የምሞተው በልጆቼ መሐል ነው፡፡ ለወባ ብዬ ክርስቶስ ያሸከመኝን መስቀል ጥዬ ልጆቼን በትኜ አዲስ አበባ አልቀመጥም፡፡
          ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ  በወባ ተይዘው ክፉኛ ታመው ሕክምና አግኝተው ሲሻላቸው  አዲስ አበባ እንዲቀመጡ  ሲመክሯቸው ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት  የሰጡት ምላሽ ነበር፡፡
          ከተማሪዎች ጋር በየጢሻው እየገቡ ሰሠሩ ጋሬጣ ልብሳቸውን ሲይዝባቸው እንኳን መለስ ብለው አያዩትም፡፡ ሲሠሩ ለልብሳቸው አይጨነቁም ነበር፡፡
          በትረ ሙሴያቸውን  በቀኝ ክርናቸው ተደግፈ ው፣ በግራ እጃቸው በትረ ሙሴውን ጫፍ ይዘው፣ መስቀላቸውን በቀኝ እጃቸው ይዘው ጫፉን  ጉንጫቸው ላይ አሳርፈው ይቆማሉ፡፡
          ሲቀመጡም በፍጹም እግራቸውን አዛንፈው ወይንም አነባብረው አይቀመጡም፡፡
          ከመንገድ ሲመጡ ልጆቻቸውን ሳያዩ አያድሩም፣ የት፣ ለምን እንደሄዱና ምን እንደተደረገ ይነግሩአቸዋል፡፡
          የሚመገቡትም ከተማሪዎች ጋር ነበር፡፡ ከተማሪዎቹ የሚለዩት በጠረጴዛ ነበር፡፡ መነኮሳት በአንድ ክፍል መጽሐፈ መነኮሳት እየተነበበላቸው ሥርዓተ አበውን እየተማሩ  ይመገቡ ነበር፡፡ በምግብ ቤቱ ድምጽ ማሰማት ፈጽሞ ክልክል ነበር፡፡ 
      ዘወትር ለደቀ መዛሙርቱ እዚህ በረሃ የወደቅኩት ሰው አፈራለሁ በማለት እንጂ አልጫ ፍትፍት ብፈልግ ከመሐል ከተማ አልወጣም ነበር፡፡ ለትምህርት ጊዜ አትስጡ፡፡ የምንኖረው በዓለም ነው፡፡ ገማቾች ጥያቄ ያቀርቡልናል፡፡ ስለዚህ በመማር ብቁ እንሁን፡፡ በማለት በዓላማ መጽናት እንዳለባቸው ያስተምሩ ነበር፡፡  ብጹእነታቸው ዘወትር ምንም ነገር ሸፋፍኖ ማለፍ አይወዱም፡፡ ቁርጥ ያለና ግልጽ ውሳኔ ይወስናሉ፡፡
          ብጹእነታቸው በዓለም መድረክ የቤተ ክርስቲያን መልእክተኛ ነበሩ፡፡ ተመራማሪና ጸሐፊ ነበሩ፡፡
          ሦስት ጃማይካውያንን በዝዋይ አስተማረው ለማዕርገ ቅስና አብቅተዋል፡፡
የብጹእነታቸው ፍሬዎች
    ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ራብዕ
    ብጹዕ አቡነ መልከ ጸዴቅ ካልእ
    ብጹዕ አቡነ ኤልያስ ሣልስ
    ብጹዕ አቡነ ያዕቆብ
    ብጹዕ አቡነ ማርቆስ
    ብጹዕ አቡነ ድሜጥሮስ
የታተሙ የብጹእነታቸው መጻሕፍቶች
 መሠረተ እምነት- ለሕጻናት ትምህርተ ሃይማኖትን ለማስተማር የተዘጋጀ
 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ
 የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ
 ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን
ያልታተሙ የብጹእነታቸው መጻሕፍቶች
 ሥርዓተ ኖሎት
 ነገረ ሃይማኖት
 ኦርቶዶክሳዊ የስብከት ዘዴ
 ቤተ ክርስቲያንህን እወቅ
 ሰላም ተዋሕዶ የተሰኘው የመዝሙር ግጥም ደራሲም ናቸው፡፡
የብጹእነታቸው ድንቅ አባባሎች
  ስለ እመቤታችን መናገር የምንችለው ስለሰውና ስለ እግዚአብሔር ስናውቅ ብቻ ነው፡፡
  የቤተ ክርስቲያን ሕይወት በመስቀል ላይ ነው፡፡ ፈተና ይበዛበታል፡፡ ስለዚህ ከግል ሕይወታችሁ ይልቅ የቤተ ክርስቲያናችሁን አቋም አጠናክሩ፡፡
 ሰው ፍላጎቱን ካላሸነፈ የእግዚአብሔር ሊሆን አይችልም፡፡
  ሥጋዊ ፍላጎቶችን ማሸነፍ ለአክሊለ ሕይወት የሚያበቃ ሰማዕትነት ነው፡፡
  ኢትዮጵያ ለእግዚአብሔር የምሥጢር ሀገር ናት፡፡
          ሐምሌ 15 ቀን 1982 ዓ.ም. በሕጻናት አምባ ( በዛሬው አላጌ ግብርና ኮሌጅ) የደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል  ቤተ ክርስቲያን መሠረት አስቀምጠው ሰው  የሚፈልገውን  ከፈጸመ የሚጠብቀው ሞቱን ነው፡፡ በማለት ብዙዎችን የሚያስገርም ነገር ተናግረው ነበር፡፡
          ሐምሌ 22 ቀን 1982 ዓ.ም. ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል ወደ መቂ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ሲሄዱ በድንገተኛ የመኪና አደጋ በተወለዱ በሃምሳ ዓመታቸው አርፈዋል፡፡
           በዕለቱ አብረዋቸው የነበሩት ዲያቆን ጳውሎስ በቀለና የመኪናው አሽከርካሪ ዲያቆን ኤፍሬም ዘውዴም በለጋ ዕድሜያቸው አርፈዋል፡፡

ለብጹእነታቸው የተደረጉ መታሰቢያዎ
    ትምህርት ቤቶች
    አዳራሾች
    ቤተ መጻሕፍት
    ሐውልት በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡


              

Thursday, July 19, 2012

ዜና መዋዕል ዘመምህር ገብረ ሥላሴ ተድላ- በሰሎሞን ወንድሙ መታፈሪያ


አባ ገብረ ሥላሴ ተድላን መጀመሪያ ያየኋቸው በ፲፱፻፸1 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በየአሥራ አምስት ቀን እሑድ ይካኼድ በነበረው የአጠቃላይ ጉባኤ መርሐ ግብር ላይ ነበር፡፡ በወቅቱ  በጣም ሕጻን በመኾኔ አባ ገብረ ሥላሴ ምን እንዳስተማሩ ትዝ አይለኝም፡፡ ነገር ግን ከጉባኤው በኋላ በዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ሲያስተምሩን ከነበሩ ወንድሞችና እኅቶች ጋር በር ላይ ሲወጡ አግኝተናቸው  በርቱ፣ በሃይማኖት ጽኑ! በማለት ጥቂት ምዕዳን ሰጥተውን ባርከውን ተለያየን፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ምክንያት በተሽከርካሪ ጋሪ(wheel chair) ላይ ተቀምጠው ሲያስተምሩ በድጋሚ አይቻቸው ነበር፡፡
   በቅብጥ ርትዕት ቤተክርስቲያን በየሩብ ዓመት በሚታተመው የጥናትና ምርምር መጽሔት ኢትዮጵያዊው አባ ገብረ ክርስቶስ በነገረ አረቢ አቡነ አብዱል መሲህ አል ሐበሻ[1]  በሚል ርዕስ  የተጻፈውን  ሳነብ እግዚአብሔር የሚያውቃቸው እኛ የማናውቃቸው በርካታ ቅዱሳን በየገዳማቱ፣ በየዱሩ፣ በየፉርክታውና በከተሞች መኖራቸው ሳይታወቅ ታላላቅ ተጋድሎ ሲፈጽሙ እንደኖሩና እንደሚኖሩ አሰብኩ፡፡  የኢትዮጵያዊው አባ ገብረ ክርስቶስ ታሪክን ለመጻፍ ሠላሳ ዓመታት መፍጀቱን ሳስብ የጸሐፊውን John Watson ጽናትና ትጋት ከልቤ አደንቅኩኝ፡፡
   ቅብጣውያን በቤተ ክርስቲያናቸው በመዳከም ላይ የነበረውን ገዳማዊ ሕይወት እንዲያንሠራራ አስተዋጽኦ ያደረጉትን የኢትዮጵያዊውን   የአባ ገብረ ክርስቶስን ታሪክ  በጽሑፍና  በዘጋቢ ምስል ወድምጽ[2] አዘጋጅተው አቅርበዋል፡፡ ቅብጣውያን ዛሬም የአባቶችን ተጋድሎ፣ ትሩፋትና አብነት ያለውን ሕይወት ያጠናሉ፣ ይጽፋሉ፣ ለምእመናንም ያስተዋውቃሉ፡፡ ይኽንን ትውፊታቸውን ሳስብ በጣም እገረማለሁ፣ በመንፈሳዊ ቅንአትም በእኛ ዘንድ ይኽንን ማድረግ የምንጀመረው መቼ ይኾን!? በማለት ራሴን እጠይቃለሁ፡፡
  በየገዳማቱና አድባራቱ ለዘመናት ሃይማኖትን ለማጽናት፣ ትምህርተ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ አምልኮተ ጣኦትን ለማጥፋት፣   መልካሙን ገድል የተጋደሉ፣ በጸሎታቸውና በትሩፋታቸው ትውልድ የታደጉ፣ ዳዋ ለብሰው፣ ጤዛ ልስው፣ ድንጋይ ተንተርሰው በመዓልትና በሌሊት ቅድመ ፈጣሪ በእንባና በስግደት ለሀገራቸው፣ ለሕዝባቸው፣ ለቤተ ክርስቲያናቸው ሲጸልዩና ሲማልዱ የኖሩ አበው ዜና ሕይወት በአግባቡ ተዘግቧል ወይንም ተጠንቷል ማለት ያስቸግራል፡፡ ዜና ሕይወታቸው የተጻፈላቸው በጣት የሚቆጠሩ አባቶች ቢኖሩም የተዘጋጁት ሥራዎች ታትመው ለሕዝብ  መድረሳቸውን ማረጋገጥ ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም የተዘጋጁት ሥራዎች በውጭ  ቋንቋ የተጻፉ በመኾናቸው ወይንም  ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተጻፉ የመመረቂያ ወረቀት በመኾናቸው አልያም የኅትመት ዕድል ባለማግኘታቸው ለሕዝብ በቀላሉ ሊደርሱ አልቻሉም፡፡
   የአንዳንድ አባቶች ዜና ሕይወት በተለያዩ መጽሔቶችና ጋዜጦች ለንባብ ቢበቃም የአባቶችን ታሪክ በማሰባሰብ በአንድነት ተጠርዞ የቀረበ ወጥ ሥራ የለም ማለት ያስደፍራል፡፡ በዲያቆን መርሻ አለኸኝ ዜና ጳጳሳት በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ በዕረፍተ ሥጋ የተለዩ ሊቃነ ጳጳሳት ዜና ሕይወት ብቻ የቀረበ እንጂ በማዕርገ ጵጵስና ያልነበሩትን ነገር ግን ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሀገርና ለወገን ታላላቅ ተግባራት ያከናወኑትን አበው ታሪክ አይዘግብም፡፡ ስለዚህም ይኽንን ክፍተት ለመሙላት ሁላችንም ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡
   @)4ዓ.ም. የታቦተ ጽዮን የስደት ዘመንና የደቡብ ከዋክብት በዛይ ደስያት የሚለውን መጽሐፍ ለኅትመት ሳዘጋጅ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ በደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ደሴት በግዞት እንደተቀመጡ ያገኘኹትን ፍንጭ መረጃ በማሰባሰብ በስፋት ለመጻፍ አሰብኩ፡፡ ወደ ደሴቱ ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብና የምስል ወድምጽ ቀረጻ ለማካሄድ በሄድኩኝ ጊዜ ከደሴተ ደብረ ጽዮን መምሬ ባንተ ይሁን ሀብተ ማርያም[3]  እንዲሁም ከደሴተ ጌተሴማኒ  አባ አሥራት መኵሪያ[4] ስለ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ የሚያውቁትን ምሥክርነት በስፋት ሰጡኝ፡፡ ሌሎች አባቶችም ያገኘሁትን መረጃ ትክክለኝነት አረጋገጡልኝ፡፡
   ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ደግሞ በአንድ ወቅት በጉባኤ ላይ መምህር ታዬ አብርሃም ስለ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲያስተምሩ አድምጬ ስለነበር ለተጨማሪ መረጃ ጥቅምት @3 ቀን @)4 ዓ.ም. ወደ እርሳቸው ዘንድ ሄጄ ነበር፡፡ የመምህር ታዬ አብርሃም  ምሥክርነት ያለምንም ዕረፍት  አምስት ሰዓት ተኩል ፈጀ፡፡ ይኽ ምሥክርነት ከሠላሳ ዓመታት በላይ በተሰበሰበ የዓይንና የጆሮ ምስክርነት ላይ የተመሠረተ ከመኾኑም በላይ ባለታሪኩ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ከልደት እስከ አረጋዊነት ዘመናቸው ያሳለፉትን ታሪክ በመምህር ታዬ በተደረገላቸው ቃለ ምልልስ በመቅረጸ ድምጽ ከተቀረጹት ታሪክ የተገኘ ነበር፡፡
     በተጨማሪም መምህር ታዬ  በቅርብ የሚያውቋቸውን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውን በማነጋገርና ሥዕለ ገጻቸውን በማሰባሰብ የተደራጀና የተጠናከረ ሥራ ሠርተው አገኘሁ፡፡ በመካከል ውይይታችን ለካስ ዛሬም በእኛ መካከል በብዙ ድካምና ጥረት፣ በብርቱ ፍላጎትና ጽናት የአባቶቻችንን ዜና መዋዕል የሚጽፉ አሉ!? በማለት ራሴን ጠየቅኩኝ፡፡
  በውይይታችን መጨረሻ ለመምህር ታዬ የዚኽ ሁሉ ድካም መጨረሻው ምንድን ነው!? የዚኽ ሥራስ ዕጣ ፈንታው ምን ሊኾን ነው!? በማለት ወቀሳ አዘል ጥያቄ  ሰነዘርኩኝ፡፡ መምህር ታዬም ያደረጉትን  ጥረት ገልጸውልኝ አንተም የድርሻህን ተወጣ፡፡ በማለት  በወቅቱ ያዩትንና የሰሙትን እንዲህም በግል ማስታወሻቸው የዘገቡትን፣ ከሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለና ከማኅበረ ሥላሴ ጸሐፊ ከአቶ ኃይለ ልዑል ሀብተ ዮሐንስ ያሰበሰቡትን መረጃ ቅጂ አስረከቡኝ፡፡ እኔም መረጃዎቹን ጊዜ ወስጄ በመመልከት ይዘቱን ሳለውጥ መጠነኛ የቅርጽና የቅደም ተከተል ለውጥ በማድረግ ብቻ የመምህር ገብረ ሥላሴ ተድላን ዜና መዋዕል ለንባብ እንዲበቃ አድርጌያለሁ፡፡
   የአባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ታሪክ ከኢትዮጵያዊው አባ ገብረ ክርስቶስ ታሪክ ጋር ተመሳሳይ ገጽታ አለው፡፡
ሀ. ታሪካቸው የተጻፈው በሕይወተ ሥጋ ከተለዩ ከሠላሳ ዓመታት በኋላ የተጻፈ መኾኑ፣
ለ. የትውልድና የአገልግሎት ዘመናቸው ተቀራራቢ መኾኑ[5]
ሐ. ሐዋርያዊ ተጋድሏቸውና ገዳማዊ ሕይወታቸው በምእመናን ዘንድ ያለመታወቁ ታሪካቸውን ተመሳሳይ አድርጎታል፡፡
  ፖውል ሄንዝ 1965 ዓ.ም.  መምህር ገብረ ሥላሴ ተድላን በደብረ ጽዮን ደሴት ተግዘው ሳለ በዚያ አግኝቷቸው የዝዋይ ሐይቅና ደስያቱ[6] በተሰኘው ጽሑፉ ላይ ሥዕለ ገጻቸውን አውጥቶት ነበር፡፡
  ይኽ መጽሐፍ ደግሞ ከሠላሳ ዓመታት በኋላ የአባ ገብረ ሥላሴ ተድላን  ትውልዳቸውና አስተዳደጋቸውን፣ የተማሪ ቤት ሕይወታቸውን ከተማሩበት አካባቢና ከመምህራኑ ሙሉ ስም ጋር ያስተዋውቀናል፡፡  በተለያዩ ገዳማትና አድባራት የነበሩትን የጉባኤ ቤቶችና መምህራንን ይነግረናል፡፡ ይኽም መጽሐፉ ለሌሎች ጥናቶች በመረጃ ምንጭነት እንዲያገለግል ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
     አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ በሕይወተ ሥጋ በነበሩበት ዘመን በቃለ መጠይቅ ታሪካቸውን እንዲተርኩ ተደርጎ በመቅረጸ ድምጽ የተቀዳው ምላሻቸው ይኽንን ዜና መዋዕል ለመጻፍ በመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ምንጭነት አግልግሏል፡፡
    ዳግመኛም ከተማሪዎቻቸው ከመምህር ታዬ አብርሃም፣ ከሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለና የማኅበረ ሥላሴ ጸሐፊ ከነበሩት ከአቶ ኃይለ ልዑል ሀብተ ዮሐንስ የተገኙ መረጃዎች በመጽሐፍ ዝግጅቱ ተካተዋል፡፡
  በመጨረሻም ተማሪዎቻቸው በየዕለቱ በተለያዩ ጉባኤያት በመገኘት በጆሮአቸው የሰሙትን የቃላቸውን ትምህርት፣ በዓይናቸው የተመለከቱትን ድርጊት በግል ማስታወሻቸው ያሠፈሩትን መረጃ እንዲሁም አባ ገብረ ሥላሴ ተድላን በቅርበት የሚያውቋቸውና በወቅቱ በተፈጸሙ የተለያዩ አጋጣሚዎች ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸውን ሰዎች በቃለ መጠይቅ በማሳተፍ  የተገኘውን መረጃ በመተንተንና በማጣራት የአባ ገብረ ሥላሴን ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በተለያዩ ጸሐፍት የተጻፉና ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን የኅትመት ውጤቶችም በማብራሪያነት በግርጌ ማስታወሻ ላይ ቀርበዋል፡፡
   የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የአበው ታሪክ በመኾኑ መጽሐፉ በአጼ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የነበረችበትንና ያለፈችበትን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ውጣ ውረድ በወፍ በረር ያስቃኛል፡፡ በዚያን ዘመን ከነበሩት ባሕታውያን እነ አባ ቸርነትን እነ ባሕታዊ ገብረ ጊዮርጊስ ትኩነህን፣ ከሰባክያን እነ አለቃ ኤልያስ ነቢየ ልዑልን በማንሣት አለባበሳቸውን አነጋገራቸውን ሳይቀር ያስተዋውቀናል፡፡ በተጨማሪም አባ ገብረ ሥላሴ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት በእግራቸው የተጓዙበትን ሥፍራ በቅደም ተከተል፣ በአድካሚውና በፈታኝ የገጠርና የከተማ የስብከተ ወንጌል የአገልግሎት ሕይወት ያሳለፉት ፈተናና የነበራቸውን መንፈሳዊ ጥብአት ያሳየናል፡፡
   መጽሐፉ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ከቤተ መንግሥት፣ ከመሳፍንቱ፣ ከቤተ ክህነት፣ ከቃልቻዎች፣ ከሴተኛ  አዳሪዎች ጋር ያረደጉት ብርቱ ተጋድሎ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት የከፈሉትን መሥዋዕትነት  በመዘርዘር ለዘመኑ ሰባክያን አብነት ያሳያል፡፡
   በተጨማሪም የሰበካ ጉባኤ ማቋቋም ያለውን ጠቀሜታ በማስረዳትና ሐሳብ በማመንጨት ያደረጉትን አስተዋጽኦ፣ ትኅርምታቸውንና ተጋድሏቸውን፣ አርቆ አስተዋይነታቸውንና ቋንቋቸውን፣ አለባበሳቸውን፣ አመጋገባቸውና ተጋድሏቸውን በዝርዝር በመግለጽ በዓይነ ሕሊናችን እንድንሥላቸው ያስችልናል፡፡ በዘመናችን የነበሩና ያሉ አባቶችን ዜና ለመጻፍም ያነሳሣል፡፡
   በመጽሐፉ ውስጥ ከሌሎች ሰዎች በቀጥታ የተወሰደ ንግግር፣ ሐሳብና ምሥክርነት በጉልህና በደማቅ ቀለም እንዲጻፉ ተደርጓል፡፡ ለአንባብያን ተጨማሪ ግንዛቤ የሚሰጡ መረጃዎች በግርጌ ማስታወሻ ላይ ተቀምጠዋል፡፡  በዋቢነት የቀረቡ ሥራዎችን   በተመለከተ በመጀመሪያ ለተጠቀሰ ምንጭ አስቀድሞ የጸሐፊውን ወይንም የአሳታሚውን ሙሉ ስም፣ ቀጥሎ የታተመበትን ዘመን፣ ከዚያም ሐሳቡ የተገኘበትን ገጽ፣ በመጨረሻም የመጽሐፉ ርዕስና የታተመበትን ቦታ የሚያሳዩ መረጃዎች በግርጌ ማስታወሻነት የተቀመጡ ሲሆን፣ ለሁለተኛ ጊዜ ወይንም በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ምንጮች ካሉ የተጻፈው የጸሐፊው ወይንም የአሳታሚው የመጀመሪያ  ስም፣ የታተመበት ዘመንና ሓሳቡ የተገኘበት ገጽ ብቻ ነው፡፡


[1]John Watson. Abdel- Mesih al Habashi(Abuna)c. 1898 to c.1973 Orthodox  Ethiopia/ Eritrea/ Egypt. In  Coptic Church Review: A Ouarterly of Contemporary Patristic studies, Vol.27, No.2 (Summer 2006).
[2] Documentary film
[3] መምሬ ባንተ ይሁን ሀብተ ማርያም በዛይ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ደሴት ተወልደው በዲቁና ዛሬ ደግሞ በቅስና የሚያገለግሉ  አባት ሲኾኑ ከአባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ጋር የቅርብ ትውውቅ ነበራቸው፡፡
[4] አባ አሥራት መኵሪያ በዛይ ደስያት ከሃምሳ ዓመት በላይ የኖሩ በዲቁና ወደ ደብረ ጽዮን ደሴት መጥተው በደሴቱ መንኵሰው ሲያገለግሉ የኖሩና ዛሬም በጌቴሴማኒ አርባዕቱ እንስሳ ቤተ ክርስቲያን በማገልገል ላይ የሚገኙ አባት ናቸው፡፡ አባ አሥራት አባ ገብረ ሥላሴ ተድላን በቅርበት ያውቋቸውና ይላላኳቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡
[5] ኢትዮጵያዊው አባ ገብረ ክርስቶስ ከ08)( ዓ.ም. እስከ 09)^5ዓ.ም. ነበሩ፡፡ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ከ08)(8ዓ.ም. እስከ 09)*2ዓ.ም. ነበሩ፡፡
[6] Paul B. Henze (1973). Lake Zway and its Islands: An Ethiopian Lake wUnique Christian Culture has Survived since medieval times. in Ethiopian Observer  Vol. XVI